የኮለኔል መንግስቱ መጽሀፍ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተቸበቸበ ነው
በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ለሶስተኛ ጊዜ ታተመ!
Ethiopia Zare (ሐሙስ ሰኔ 7 ቀን 2004 ዓ.ም. june 14, 2012)፦ በጸሐይ አሳታሚ ድርጅት የታተመው እና በቀድሞው የኢትዮጵያ ፕ/ት በኮለኔል መንግስቱ ኀ/ማርያም የተጻፈው 'ትግላችን' የተሰኘው መጽሀፍ የመጀመሪያ ክፍል ኢትዮጵያ ውስጥ ታትሞ በስፋት እየተሰራጨ ሲሆን በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ ለሶስተኛ ጊዜ መታተሙን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች በተለይ ለኢትዮጵያ ዛሬ ገለጹ።
እንደ ኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ከሆነ በአገር ቤት የታተሙት ሁለት እትሞች በከፍተኛ ፍጥነት ተሽጠው ማለቃቸው ሲታወቅ ዕድሉን ባላገኙ አንባቢያን ጥያቄ መሰረት ለ3ኛ ጊዜ የቀረበው ዕትምም ቢሆን የመጨረሻው እንደማይሆን በስፋት ከሚስተዋለው የአንባቢያን ጉጉት ለመረዳት አይገድም ብለዋል። "ትግላችን" በየመፅሀፍት መደብሩ በአንድ መቶ የኢትዮጵያ ብር ሂሳብ ሲሸጥ የቆየ ቢሆንም ከመደብሮች ውጪ ግን አዟሪዎች ከዚያም በላይ ዋጋ እያስከፈሉ ሲሸጡ እንደነበር አንዳንድ ያነጋገርናቸው ምንጮች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
መጽሀፉን ያሳተመው "ፀሀይ አሳታሚ ድርጅት" በአቶ ኤሊያስ ወንድሙ የተመሰረተና በአሜሪካን ሀገር የሚገኝ ሲሆን ባለፉት አስር ዓመታት ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያንና የአፍሪካን ባህልና ታሪክ የሚያስተዋውቁ፤ በታዋቂ ምሁራንና ተመራማሪዎች የተጻፉ ከሀምሳ በላይ አለማቀፍ ደረጃዎችን የጠበቁ መጻህፍትን በማሳተም ታላቅ እውቅናን ያተረፈ ድርጅት ነው።
የ"ትግላችን" ደራሲ ኮለኔል መንግስቱ ኀ/ማርያም ለአስራ ሰባት ዓመታት ያህል ኢትዮጵያን የመሩ አምባገነን ፕሬዘዳንት ሲሆኑ ህወሀት መራሹ ኢህአዲግ ወደ አዲስ አበባ በገሰገሰበት በ1983 ዓ.ም. ወደ ዚምቧቤ መሰደዳቸው ይታወቃል። በኮለኔሉ አገዛዝ ስር እጅግ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ያለፍርድ ሲገደሉ፣ ሲታሰሩና ሲደበደቡ ከመኖራቸውም በላይ ፍፁም አምባገነን በሆነው መንግስታቸው ስር መላው ህዝብ ነጻነቱን ተነፍጎ በምሬት ያሳለፈበት የታሪካችን ጠባሳ ዘመን ስለመሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ። በዚህም መፅሀፋቸው ለንባብ ሲበቃ በበርካታ አንባቢያን ዘንድ የመነጋገሪያ ርዕስ ለመሆን የቻለ ሲሆን ባንድ ወገን "መፅሀፉ የወቅቱን ትክክለኛ ድርጊት የሸፋፈነና ኮለኔሉ የራሳቸውን ስምና ዝና ጠብቀው ከታሪክ ተወቃሽነት ለመዳን የተፍጨረጨሩበት ነው" የሚሉ ሰፊ ትችቶች ሲቀርቡበት በሌላ ጎኑ ደግሞ "ኮለኔሉ የተዋጣለት የመፃፍ ችሎታ እንዳላቸው ያሳዩበትና ለተወሰኑ ጥያቄዎችም ቢሆን ምላሽ ሊሰጡ የቻሉበት ነው" የሚሉ ወገኖችም የተደመጡበት ሁኔታ ታይቷል።
መጽሀፉ በአገር ቤት ከመታተሙ አስቀድሞ በውጪ አገራት ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የንባብ ፍጆታ እንዲውል ባለፈው የታህሳስ ወር በሎስ አንጀለስ መታተሙ ሲታወስ በወቅቱ ለዲሞክራሲና ሀሳብን በነጻነት ለመግለፅ መብት እንደሚታገል ከሚገልጸው የኢትዮጵያ ህዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) አንደኛው ክንፍ ጋር ራሱን ያቆራኘ አንድ ድረ-ገፅ መፅሀፉን ሙሉ ለሙሉ 'ስካን' አድርጎ በመልቀቁ ከፍተኛ ውግዘት ገጥሞት እንደነበር ይታወሳል።
አሳታሚ ድርጅቱ በመግቢያ ማስታወሻው "የግለሰቦች የመጻፍና የመናገር መብት ለአንዱ ተለግሶ ለሌላው የሚከለከል አይደለም" ሲል እንደገለፀው ሁሉ 'ህዝብ የማወቅ መብት አለው' የሚሉ በርካታ ወገኖችም የማንበብም ሆነ ያለማንበብ፣ የመቀበልም ሆነ የመተቸት መብት ለዜጎች የሚሰጥ እንጂ "እኔ ከምለው ሌላ አትስሙ፣ ለእኔ የማይመቸኝን መፃፍም ሆነ ማተም አትችሉም" የሚል አፋኝ ማስፈራሪያ በሚያቀርቡ ቡድኖች ከቶም ሊታፈን የሚገባው አይደለም ሲሉ መኮነናቸውም ይታወሳል።
ባሁኑ ወቅት በአገር ቤት በስፋት እየተሰራጨ ያለው "ትግላችን" መጽሀፍ ኮለኔል መንግስቱ ለንባብ አበቃለሁ ካሉት ሶስት ቅፅ መጻህፍት የመጀመሪያው ሲሆን ተከታዮቹ ሁለት ክፍሎች በመጪዋቹ ዓመታት ለንባብ ይበቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።



