እነ እስክንድር ነጋ አለም በቃ ይጠብቃቸዋል
ጥፋተኛ ናችሁ የሚል ብይን ተሰጥቷል
Ethiopia Zare (ረቡዕ ሰኔ 20 ቀን 2004 ዓ.ም. june 27, 2012)፦ በእነ አንዷለም አራጌ የክስ መዝገብ ከአወዛጋቢው የሽብርተኝነት አዋጅ ጋር በተያያዘ ከመስከረም ወር ጀምሮ በማሰቃያነቱ በሚታወቀው የማእከላዊ እስር ቤትና በቃሊቲ ወህኒ ቤት የቆዩት 24 ተከሳሾች ላይ የጥፋተኝነት ብይን ተሰጠ።
ዛሬ ረቡዕ በዋለውና በመጥፎነቱ በሚታወቀው የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት ከተከሰሱት 24 ተከሳሾች ውስጥ ስምንቱ ብቻ የቀረቡ ሲሆን በዳኛ እንደሻው አዳነ የተመራው የከፍተኛው ፍርድ ቤት የ3ኛ ወንጀል ችሎት ብይኑን አስተላልፏል። ተከሳሾች በሚቀጥለው ቀጠሮ የእድሜ ልክ እስራት ውሳኔ እንደሚጠብቃቸው ተገምቷል።
ፍርድ ቤቱ በእስኞች ቤተሰቦች፣ በጋዜጠኞችና በዲፕሎባቶች ተጨናንቆ የነበረ ሲሆን በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ዶናልድ ቡዝና ሌሎች ከፍተኛ ዲፕሎማት እንደተገኙ ለማወቅ ተችሏል።
እስክንድር ነጋና አንዷለም አራጌን ጨምሮ ሌሎች ተከሳሾች ጥፋተኛ ሆነው የተገኙት አሸባሪ ድርጅት ተብሎ በህወሀት መራሹ የኢትዮጵያ መንግስት የተሰየመው ግንቦት 7 ድርጅት ጋር ግንኙነት በመፍጠርና በሀገሪቱ ውስጥ ሽብር ለመፍጠር በማቀዳቸው መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ የአረብ ስፕሪንግን ስሜት በሀገሪቱ ለማስነሳት ቅስቀሳዎችን አድርገዋል የሚል እርስ በርሱ የማይስማማ የውንጀላ ክስ እንደተጠቀሰባቸው ተገልጿል።
አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች አምንስቲ ባወጣው መግለጫ ውሳኔው ቀድሞ የተወሰነበት መሆኑን ጠቅሶ እስረኞቹ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጥሪ አቅርቧል።
“ዛሬ ለኢትዮጵያ የፍትህ ጨለማ ቀን ነው” ያሉት የአምንስቲው የአፍሪካ የጥናት ቡድን ባልደረባ የሆኑት ክሌይር ቤስተን “የመናገር ነጻነትን መንግስት በተለያየ ዘዴ በመጠቀም እያጠፋ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
አንዷለም አራጌ ሙሉ ልብስ በመልበስ ፍርድ ቤት የቀረበ ሲሆን በንግግሩም “የእኔ አላማ ግልጽ ነው በሰላማዊ ትግል የተሳተፍኩና ምንም አይነት ወንጀል ያልፈጸምኩ ሁሉንም የማከብር ነኝ” ሲል መናገሩ የታወቀ ሲሆን ዳኛው በአስቸኳይ አስቁሞታል።
ጋዜጠኛና የፖለቲካ ተንታኝ የሆነው እስክንድር ነጋ ደግሞ የመናገር መብቱ እንዲጠበቅለት ከማሳሰቡም በላይ የሚጠብቀው ፍርድ አደገኛ መሆኑን ተናግር “ለፍትህ መቆም ይገባችኋል፣ መናገር ምንፈልገውን መፍቀድ አለባችሁ፣ የመናገር መብታችንን አትገድቡ” ሲል ለዳኞች ማሳሰቡ ተጠቅሷል።
የተሰጠው ብይን በብዙ የህግ ባለሙያዎች፣ የፖለቲካ ተንታኞችና አለም አቀፍ ተቋማት በሆኑ ታላላቅ ድርጅቶች ዘንድ እየተወገዘ ሲሆን በተለይ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቾችና የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች የብይን ሂደቱ በተሰጠ ሰዓት ጀምረው ውሳኔውን በማውገዝ ተቃውሟቸውን ማሰማታቸው ተመልክቷል።



