Ethiopia Zare (ማክሰኞ ግንቦት 26 ቀን 2000 ዓ.ም. June 3, 2008)፦ ከመርዛማ ዕፁ ጋር የምግብ ዘይት ቀላቅለው ሲያመርቱ የነበሩ 16 የዘይት መጭመቂያ ቤቶች መታሸጋቸውን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የድርጊቱ ፈፃሚዎች እስካሁን እንዳልተደረሰባቸውና ፋብሪካዎቹ ስለመታሸጋቸውም መረጃ እንደሌላቸው ገልጿል።

 

ማክሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2000 ዓ.ም. ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የጤናና የሥነ-ምግብ ምርመር ኢንስቲቲዩት ጋር በሰጠው መግለጫ 16 የዘይት መጭመቂያ ቤቶች መታሸጋቸውንና ሁለት የዘይት ፋብሪካ ባለቤቶች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ህዝብ ግንኙነት አቶ አሕመድ ኢማም ተናግረዋል።

 

ይሁንና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ህዝብ ግንኙነት ኢንስፔክተር አብርሃም ዘለቀ፤ ፋብሪካዎች ስለመታሸጋቸው የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ለሀገር ውስጥ ሚዲያ ገልፀው፤ ነገር ግን በመርካቶ ጉራንጉር ውስጥ በበርሜልና በ20 ሊትር ቢጫ ጀሪካን የታሸጉ የተበከሉ ዘይቶችን ሲሸጡ የነበሩ የተለያዩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።

 

በርካታ በቢጫ ጀሪካን የታሸጉ ከመርዛማ ፍሬ ጋር የተቀላቀሉ ዘይት መሰል ነገር በአይሱዙ እንደተጫነ በቁጥጥር ስር መዋሉን ኢንስፔክተሩ ጨምረው ገልፀዋል። መርዛማው ፍሬ “መዳፌ” በመባል ከሚታወቀው ተክል (በሣይንሳዊ አጠራሩ ‘አርጂሞን ሜክሲካና’ Argemone Mexicana) የሚገኝ ሲሆን፣ ከዚህ ፍሬ ተጨምቆ የሚገኘው ዘይት ለሰውና ለእንስሳት በምግብነት መዋል የሌለበት እንደሆነ ታውቋል። ሰው በምግብነት ከተጠቀመበት እስከ ለአራት ቀናት ምንም ችግር ሳያስከትል ከቆየ በኋላ ለሞት ሊዳርግ እንደሚችል ተረጋግጧል።

 

የአዲስ ጤና ቢሮ የበሽታዎች መከላከልና ጤና ፕሮግራሞች መምሪያ ኃላፊ ዶክተር አቻምየለህ አለባቸው እንደገለጹት፤ አላስፈላጊ ትርፍን ለማካበት ከመርዛማ ፍሬ ጋር ዘይትን በመቀላቀል የሸጡ ነጋዴዎች ራሳቸውም ሆስፒታል እንደሚገኙ ጠቁመው በበሽታው የተጠቁ ሰዎች በተለይ ከኮሌፌ ቀራኒዮ፣ ከልደታ፣ ከጉለሌና ከአዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች ብዛት ያላቸው በሽተኞች በተለያዩ ሆስፒታሎች እንደሚገኙ ተናግረዋል።

 

ለምግብነት መዋል የማይችለው ይኸው መርዛማ ተክል፣ ለአራት ቀናት በሰውነት ውስጥ ምንም ለውጥ ሳያስከትል መቀመጥ የሚችል ሲሆን፤ የበሽታው ስርጭት በሰውነት ሲስፋፋ እስከሞት እንደሚያደርስ በጋዜጣዊ መግለጫው ተገልጿል።

 

መርዛማ ዕፁን ከዘይት ጋር የተመገቡ 66 ሰዎች ሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2000 ዓ.ም. ጳውሎስ ሆስፒታል የገቡ ሲሆን፣ በማግስቱ ቁጥራቸው በ15 ጨምሯል። ዕድሜያቸው ከ4 እስከ 15 የሚሆኑ 19 ሕፃናቶች ደግሞ አልጋ ባለማግኘታቸው ወደ ጥቁር አንባሳ ሆስፒታል ተልከዋል።

 

በአሁኑ ሰዓት የተበከለው መርዛማ ዘይት ስርጭት ጎልቶ የታየው በአዲስ አበባ ብቻ ሲሆን፣ ከአዲስ አበባ 54 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው አዲስ ዓለም ከተማ የመጡ ሕመምተኞችም በጥቁር አንበሳ እንደሚገኙ ታውቋል።

 

በአጠቃላይ ለስምንት ሰዎች መሞት ምክንያት የሆነው ይኸው መርዛማ ተክል 94 ሰዎችን ደግሞ የሆስፒታል አልጋ እንዲይዙ አድርጓል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ