በጅምላ መቀበራቸው ቀይ መስቀልን አሳስቦታል

ስድስት ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በተአምር ተርፈዋል!!

Ethiopia Zare (ማክሰኞ ሐምሌ 3 ቀን  2004 .. july 10, 2012)፦ ባለፈው ወር መጨረሻ ላይ ወደ ደቡብ አፍሪካ በማምራት ላይ የነበሩ ኢትዮጵያውያንን የጫነች ጀልባ በማላዊ ሃይቅ ላይ በመገልበጧ 47 ኢትዮጵያን ወንዶች፣ ሴቶችና ሀጻናት መሞታቸው ሲታወስ በወቅቱ በእካባቢው ነዋሪዎች አማካኝነት ከሃይቁ ዳርቻ ጥቂት ሜትሮች ርቀት ላይ በተቆፈረ ጉድጓድ ውስጥ በጥድፊያ እንዲቀበሩ በመደረጋቸው ለሟቾቹ ክብር ያልሰጠ ሂደት ነው በሚል ቀይ መስቀል እንደ አዲስ ተገቢ ቀብር እንዲፈጸምላቸው ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን ዘ ሰንዴይ ታይምስ የተሰኘ የአገሪቱ ጋዜጣ ዘግቧል።

ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች በታንዛንያ በኩል ህገ-ወጥ በሆነ ሁኔታ ወደ ማላዊ ያቋረጡት በጀልባ ሲሆን የጉዞአቸው አላማም በሞዛምቢክ ተሻግሮ ደቡብ አፍሪካ መድረስ ነበር ተብሏል። ይሁንና 28 ሰዎች ብቻ የመጫን አቅም ነበራት የተባለችው ጀልባ ላይ ወደ 60 የሚጠጉ ስደተኞች በመጫናቸው ጀልባዋ መገልበጧ ነበር በወቅቱ የተዘገበው።

             ከማላዊ መዲና በ600 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ካራንጎ በተባለችው የወንዝ ዳር መንደር የሚገኙ ነዋሪዎች በሀይቁ ላይ የሚንሳፈፉ አስክሬኖች አይተው ለፖሊስ ሪፖርት በማድረጋቸው 47 ያህል የኢትዮጵያዊያን ስደተኞች አስክሬን ለመገኘት የቻለ ሲሆን ዘግይቶም በአስገራሚ ሁኔታ 6 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በህይወት ሊገኙ መቻላቸው ተመልክቷል።

             የሟቾቹን ስደተኞች የቀብር ሁኔታ በተመለከተም ሆነ የተረፉትን ኢትዮጵያውያን ለመርዳት በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የተደረገ ጥረት ባይኖርም በጥድፊያ ባንድ ጉድጓድ ውስጥ 47 ኢትዮጵያውያን መቀበራቸው ያሳሰበው የማላዊ ቀይ መስቀል ግን ለሟቾቹ ክብር በሚሰጥ መልኩ ወግ ያለው ቀብር ሊያስፈጽምላቸው ሙከራዎች እያደረገ መሆኑ ታውቋል።

              የማላዊ ቀይ መስቀል የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆኑት ሆሬስ ኒያካ ለሰንደይ ታይምስ እንደገለጹት ከሆነ ተገቢውን ቀብር ለማስፈጸም ስለሚቻልበት ሁኔታ ቀይ መስቀል ከፖሊስና ከአካባቢው ባህላዊ አለቆች ጋር እየመከረበት ይገኛል። ይሁንና ይህን እቅድ ለማስፈጸም የሚያስፈልገውን ወጪ ማን ሊሸፍነው እንደሚችልም ሆነ የማላዊና የኢትዮጵያ መንግስታት ትብብር ይታከልበት እንደሆነ ክጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ሃላፊው ምላሽ ለመስጠት አልቻሉም።

              « የካራንጎ ባለስልጣናትም ሆኑ የአካባቢው ፖሊስ ይህን መሰል ሁኔታ አጋጥሟቸው ስለማያውቅ የጅምላ ቀብርን በተመለከተ ምን ማድረግ እንደሚገባቸው በወጉ የሚያውቁት ነገር አልነበረም።» የሚሉት ሆሬስ ኒያካ በወቅቱ ፖሊስ አቅሙ በፈቀደ ልክ ያገኘውን የሰውና የገንዘብ ህይል አስተባብሮ የሚችለውን በማድረጉ ሊመሰገን ይገባዋል ብለዋል። በተመሳሳይ መልኩም የካራንጎ ነዋሪዎችና የወረዳው ኮሚሽነር ቢሮም ዘግናኙን እልቂት ተከትሎ ያደረጓቸው የአጸፋ ጥረቶች ያስመሰግናቸዋል ያሉት እኚሁ የቀይ መስቀል ሹም መ/ቤታቸው ለሟቾቹ ተገቢ ቀብር ለማስፈጸም ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪ ስደተኞቹን በተመለከተ እየሰሯቸው ያሉትን ተግባራትም ዘርዝርዋል።

               የማላዊ ቀይ መስቀል የሟቾቹን ማንነት ለመለየትና ለዘመዶቻቸው እውነቱን ለማሳወቅ እስካሁን እየሞከረ መሆኑንም አመላክተዋል። በአደጋው ወቅት በአስገራሚ ተአምር ከሞት የተረፉት ስደስቱ ኢትዮጵያውያንም የሟቾቹን ማንነት ለመለየት እገዛ ማድረጋቸው የተጠቀሰ ሲሆን ከሟቾቹ አንዳንዶቹ የዘመዶቻቸውን ፎቶዎች በኪሳቸው ይዘው መገኘታቸውም ጠቃሚ እንደነበር ተዘግቧል። ባኳያውም ተራፊዎቹን ስድስት ኢትዮጵያውያን በተመለከተ አገር ቤትም ሆነ በሌላው አለም ከሚኖሩ ዘመዶቻቸው ጋር መገናኘት እንዲችሉ ቀይ መስቀል ባለው የሰዎች ማፈላለጊያ ፕሮግራሙ አማካኝነት ጥረት እያደረገ መሆኑ ተወስቷል።

                ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ችግር ሳቢያ አገር ጥለው የሚሰደዱት ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ የመጣ ሲሆን በተለይም የመንና ደቡብ ሱዳንን ጨምሮ ወደሌሎች ደሃ ወደ ሆኑ አገራት ሳይቀር የሚሰደደው ዜጋ ከፍተኛ ቁጥር ያለው መሆኑ ኢትዮጵያ ዛሬ ለዜጎቿ ምን ያህል ተስፋ አስቆራጭ አገር የመሆኗ አመልካች ነው ሲሉ ብዙ ሰዎች ይተቻሉ።

           አብዛኛዎቹ በጎረቤት አገራት በኩል የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን የሚያመሩት ወደ ደቡብ አፍሪካ መሆኑ ሲታመን በየመንገዱ በተለያዩ አደጎች የሚሞቱትና በስደት አቀናጆች በኩል እንግልት የሚደርስባቸው ኢትዮጵያውያን ዜናም እየተለመደ ከመጣ ቆይቷል። በማላዊ የተለያዩ እስር ቤቶች ውስጥ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እንደማይጠፉ የሚነገር ሲሆን በተለይም በ2007 ዓ.ም በነዳጅ መጫኛ ቦቴ ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን ታጭቀው ወደ ሞዛምቢክ ሊያቋርጡ ሲሞክሩ ተይዘው እንደነበር አይዘነጋም።

           በተመሳሳይ ሁኔታም  ባለፈው ወር በኬኒያ በኩል ረዥሙን የደቡብ አፍሪካ ጉዞ በከባድ መኪና ውስጥ ታጭቆ ለማለፍ መንገድ ከጀመሩ ኢትዮጵያውያን መሃል አርባ ሶስቱ ታንዛኒያ ውስጥ ታፍነው በመሞታቸው እዛው የጅምላ ቀብር ሲፈፀምላቸው የተረፉት ለእስር እንደተዳረጉ መዘገቡ ይታወሳል። በየአረብ አገራቱም እንዲሁ በተለይም ሴቶች እህቶቻችን በአሰሪዎቻቸው ከመንገላታት አልፎ በተለያዩ መንገዶች ለሞት እየተዳረጉ ቢሆንም ይህን ሁሉ መከራ እያወቁም ቢሆን በየእለቱ ከዚህ አይብስም በሚል አገራቸውን ለቀው ወደ አደጋ የሚስደዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ግን መጨመሩን አላቆመም።

            የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎች የመኖር ዋስትና አጥተው ካገር እንዲባረሩ ምክንያት ክመሆኑ ባሻገር በየስደት ምድር ለሚደርስባቸው በደልም ሆነ በአሳዛኝ ሁኔታ እልቂት ከደረሰባቸው በኋላ እንኳ ያገባኛል በሚል አንዳችም እንቅስቃሴ ሲያደርግ ያለመታየቱ አገዛዙ ምን ያህል በጭካኔ የተሞላና የኢትዮጵያዊነት መንፈስ የሌለው ለመሆኑ ማረጋገጫ ነው ሲሉ ብዙዎች ይስማማሉ።

      

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ