ጁላይ 28 አምስት የፖለቲካ ድርጅቶች ለውይይት ተጋበዙ
”ቃሌ” የተሰኘው የፓልቶክ የፖለቲካ መወያያ ክፍል ጁላይ 28 ቀን 2012 እ.ኤ.አ. ”ጥምረት ለነፃነት ለእኩልነትና ለፍትህ በኢትዮጵያ”ን፣ ”ኦሮሞ ነጻነት ግንባር”ን፣ ”የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ”ን፣ ”የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ”ን እና ”የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሽግግር ምክር ቤት”ን በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ለውይይት መጋበዙን ለኢትዮጵያ ዛሬ ገለጸ።
”ቃሌ” ፖለቲካ የውይይት ክፍል የአምስቱን ፓርቲዎች መሪዎችና አባላቶች እንዲሁም ኢትዮጵያውያንን በውይይቱ ላይ እንዲካፈሉ መጋበዙን ለኢትዮጵያ ዛሬ ገልጿል። ቃሌ ያስተላለፈውን ሙሉውን የውይይት ጥሪ ከዚህ በታች እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
ለተከበራችሁ፡
የጥምረት ለነጻነት ለእኩልነትና ለፍትህ በኢትዮጵያ
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር
የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ
የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሽግግር ምክር ቤት
መሪዎችና አባሎች፤
ጉዳዩ፤ ቃሌ (የብርቱካን ሚደቅሳ) የፖለቲካ መወያያ ክፍል ውስጥ በጁላይ 28 ቀን 2012. ኤም ኢስተርን ታይም ወይንም በ20 ሴንትራል ዩሮፒያን ታይም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉዳይ ላይ አስተያየታችሁን እንድትሰጡ በክብር ተጋብዛችሗል።
የቃሌ ታዳሚዎች ስለ ኢትዮጲያ ፖሌቲካ ውይይት የጋበዟችሁ ለጁላይ 28 ቀን 2012 ቢሆንም፣ ሌሎች እህት ክፍሎች፤ ከረንት አፌይርስ፣ አበራሽ በርታ፣ አሉላ አባነጋና ለሌሎቹም ውይይቱን መከታተል ለሚፈልጉ ለማሰማት ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ እንዲቻል የሚመጡትን የተወካዮቻችሁን ስም የሚገልጽ የኢሜል መልስ ይህ ኢሜል ወደመጣበት አድራሻ ከጁላይ 26 ቀን 2012 በፊት በመላክ እንድትተባበሩን እየጠየቅን፣ ተወካይ ለመላክ የማትችሉ ከሆነ ደግሞ ከጁላይ 26 ቀን 2012 በፊት በኢሜል እንድትገልጹልን በአክብሮት እንጠይቃለን።
በመጀመሪያ ቃሌ (የብርቱካን መዴቅሳ)፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ መወያያ ክፍል ዓላማ ጸረ-ወያኔ አቋም ያለን ኢትየጵያውያን እንዴት ፍትሕ፣ የግለሰብ ነጻነትና ዲሞክራሲ የሰፈነባት ኢትዮጵያን ማምጣት በሚቻልበት ጉዳዮች ላይ እንድንወያይ ማድረግ ነው። ለዚህም የክፍሉ አድሚኖች በዚሁ ዓለማ የሚያምኑና የተለያየ የፖለቲካ ድርጅት ደጋፊዎችና እንዲሁም ደግሞ የምንም ድርጅት መስመር ተከታዮች ያልሆኑም ይገኙበታል።
ለክፍሉ ታዳሚዎች፣ የወያኔን ፖለቲካ ማራመድ ከሚጥሩት በስተቀር፣ ውይይቱ ላይ ሃሳባቸውን በነጻ እንዲገልጹ መድረኩ ክፍት ነው። ቃሌ እንደውይይት መድረክ የማንም የፖለቲካ ድርጅት ፕሮፓጋንዳ አይካሄድበትም። በተቃዋሚና በጸረ-ወያኔ ፖለቲካ የሚታወቅ የፖለቲካ ድርጅትም ሆነ ግለሰብ ወይንም የድርጅት መሪ አይዘለፍበትም።
በኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው ፖለቲካ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ኢትዮጵያውያን ለውይይት በሚቀርቡት የውይይት ርእሶች ላይ የግራም ሆነ የቀኝ አመለካከት ይኑራቸው፣ ወይንም ደግሞ ይሄንን ድርጅት አልደግፍም በማለታቸው ከውይይት አይታቀቡም። ከውይይት የሚታቀቡት በዘለፋ፣ በስም ማጥፋት እንዲሁም ከተያዘው የውይይት ርእስ እየወጡ ሲያስቸግሩ ብቻ ነው። የመሳተፍ መብታቸው ለአጭር ጊዜ ብቻ ይወሰድባቸዋል። የቃሌ አድሚኖችና ታዳሚዎች በአማካይ ቀን ለውይይት እሰከ 110 ሲደርሱ፣ ለየት ባሉ ቀናት ደግሞ ከ250 በላይም በመሆን ሁለተኛ ክፍል እሰከመክፈትም የሚደረስበት ጊዜ አለ። እንደ ጁላይ 28 ቀን 2012 ባለው ሰፊ ዝግጅት ወቅት ደግሞ አህት ክፍሎች ከረንት አፌርስ፣ አበራሽ በርታ፣ አሉላ አባነጋና ሌሎቹም ውይይቱን እንዲያሰተላልፉ ሲደረግ የታዳሚው ብዛት ከ800 በላይ ይሆናል ብለን እንገምታለን። ይህ እንግዲህ ቃሌን በሩቁ ለምታውቁ ባጭሩ ግልጽ እንዲሆንላችሁ ለማድረግ ነው።
በዚህ ባሳለፍናቸው ጥቂት ወራት ኢትዮጵያውያን ባገር ውስጥና ከኢትዮጵያ ውጭ በዲሞክራሲና በፍትሕ ዙሪያ በሚከተሉት ተግባራዊና ፖሌቲካዊ ሂደት ውስጥ በከፍተኛ ፍጥነት እየተጓዙ ይገኛሉ፤
• በጋምቤላ፣ በአፋር፣ በኦጋዴንና በበጌምድር ሕዝቡ ለነጻነቱ በተለያየ መንገድ እየተናነቀና እይተዋደቀ ነው።
• ሙሰሊም ዜጎቻችን ለእምነት ነጻነታቸው በየሳምንቱ ድምጻቸውን በማሰማት እየታሰሩና እየተገደሉ ይገኛሉ።
• መምሕራን፣ ጋዜጠኞች፣ እንዲሁም ሰላማዊ ታጋዮች የነጻነት ያለህ በማለታቸው ከስራ በመባረርና በሽብርተኛነት እስከእድሜልክ እስራት እየተበየነባቸው ናቸው።
• አቶ መለስ ዜናዊ አንዴ ታመዋል፣ አንዴ እረፍት ሄደዋል በሚል ሊተኳቸው የሚችሉትንም የሕወአት/ኢሕአዴግ መሪዎች ስም በተለያየ መንገድ በማስወራት ሕወአት በአንድ በኩል የአቶ መለሰን መገለል በሌላ በኩል ሌሎች የሚተኳቸው መሆኑን ቀስ በቀስ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲቀበለው በማለማመድ ላይ ይገኛል።
• በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የሰላማዊ ትግል የሚያካሂዱ የፖሌቲካ ድርጅት መሪዎች ደግሞ ጊዜው የሚጠይቀው የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉ የአገር ማዳን ስብስብ ማድረግ አለባቸው እያሉ ነው።
• በውጭ አገር ያሉ የኢትዮጵያ ፖሌቲካ ድርጅቶችና ኢትዮጵያውያን፣ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ በወያኔ ላይ በሚወሰደው ፖለቲካዊ እርምጃ ሁሉ ትብብር እያሳዩ ነው። የፖሌቲካ ድርጅቶች የጋራ ግንባሮች ተፈጥረዋል፣ የሽግግር ምክር ቤትም ተመስርቷል። የኢትዮጵያ ዲያስፖራም የፖሌቲካ ድርጅቶች ተሰባስበው ስለኢትየጵያ መነገጋር ያለባቸው ጊዜው አሁን በሚል በየመድረኩ ሲነጋገር ይሰማል።
ከየድርጅቶቻችሁ በጁላይ 28 ቀን 2012 ቃሌ የመወያያ ክፍል የምትልኳቸው ተወካዮች ከዚህ በታች በተዘረዘሩት ሶሰት አበይት ጉዳዮች ላይ የድርጅቶቻችሁን እምነትና አስተያየት እንዲያካፍሉን በከፍተኛ ጉጉት እንጠብቃለን፤
1. የሃገሪቱ ወቅታዊ ፖለቲካ አየር ምን ይመስላል? ሕወአት/ኢሕአዴግ ከመለስ በዃላ እመርታዊ ተሃድሶ ሊያመጣ ይችል ይሆን?
2. በተቃዋሚ ጎራ ያሉ የፖሌቲካ ቡድኖች መሰባሰብና ስለወደፊቷ ኢትዮጵያ መነጋገር አያስፈልግም? ተሰባስቦ ስለሀገር መወያየት አያስፈልግም ከተባለ ደግሞ ምክንያቱ ምን ይሆን? ተሰባስቦ መነጋገር ካሰፈለገ ደግሞ የዚህ ተሰባስቦ መወያየት ጥቅሙ ምንድን ነው?
3. የመለስን መገለል ተከትሎ፣ የምእራብ አገሮች በፖለቲካ ስልጣን ዙሪያ እናደራድራችሁ ቢሉ፣ ሊሆን የሚችለው ምንድን ነው? የፖለቲካ ቡድኖች ወይንም ግንባሮች በተናጠል የሚደራደሩበት ሁኔታ ሊኖር ይችል ይሆን? በተናጠል የሚደራደሩ ከሆነ ደግሞ ከሕዝቡ የነጻነትና የፍትሕ ጥያቄ ጋር እንዴት ሊያያዝ ይችላል?
ውይይቱ ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ያለበት ሆኖም መጠየቅ ያለባቸው ጥያቄዎች ከታዳሚው በአክብሮት ስለሚጠየቁ ተወካዮቻችሁ ተገቢውን መልስ ባለመሰልቸት እንደሚሰጡ እንተማመናለን።
ከአክብሮት ጋር
የቃሌ (ብርቱካን መዴቅሳ) የኢትዮጵያ ፖለቲካ መወያያ ክፍል አድሚኖችና ታዳሚዎች



