ደራሲ ገጣሚና ባለቅኔ ኃይሉ ገብረዮሃንስ እና ጋዜጠኛ አህመድ አሊ ተሸላሚ ሆኑ

ማትያስ ከተማ

ደራሲ ገጣሚና ባለቅኔ ኃይሉ ገብረዮሐንስ

Ethiopia Zare (ሐሙስ መስከረም 3 ቀን 2005 ዓ.ም. September 13, 2012) የኢትዮጵያን አዲስ ዓመት አንተርሶ የምስረታ በአሉን በየዓመቱ የሚአከብረው የኢትዮጵያ ድምጽ ራድዮ አስራ ዘጠነኛ አመቱን በርካታ ኢትዮጵያውያን ታዳሚዎች በተገኙበት ቅዳሜ ሴፕቴንበር 8,2012 (ጳጉሜ 3,2004 ዓ.ም) አከበረ። በበአሉ አከባበር ላይ ደራሲ ገጣሚና ባለቅኔ ኃይሉ ገብረዮሃንስን በክብር እንግድነት የተገኙ ሲሆን የተዘጋጀላቸውንም የክብር ሽልማት ተቀብለዋል።

 

ለጋዜጠኛ አህመድ አሊ ደግሞ ከራድዮኑ ምስረታ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ላደረጉት አገልጐት የምስጋናና የክብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።በተጨማሪም ከአሜሪካንና ከእንግሊዝ የመጡት ድምጻዊ ተሾመ አሰግድና ድምጻዊት የዝና ነጋሽ በዓሉን የደመቀ አድርገውት ውለዋል።

 

ዝግጅቱ ረፋዱን ከ13፡00 ጀምሮ በምሳ ግብዣ የተጀመረው ሲሆን የዝግጅቱን መክፈቻ ያደረጉት የኢትዮጵያ ድምጽ ሬድዮ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ እንዳለ ወ/ስላሴ ናቸው ። አቶ እንዳለ በንግግራቸው የሬድዮኑን የስራ አገልግሎትና ለተጠቃሚው ያደረገውን የስራ ፍሬ ገልጸው ሬድዮ ለየት ብሎ እንዲታይ የሚአደርገው ደግሞ ዘርፈ ብዙ በሆነው ዝግጅቱ እንደሆነ ጠቁመዋል።በማያያዝም ህብረተሰቡ ያላቋረጠ ድጋፍ በማድረጉ አመስግነው ለወደፊቱም ይኸው ድጋፉ ሳያቋርጥ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

 

 

ከአቶ እንዳለ ንግግር ማብቂያ በኋላ የዝግጅቱ መሪ ወ/ሮ እመቤት ፋንታሁን ዝግጅቱ ምን አይነት መልክ እንዳለው አሳውቀው ዝግጅቱን የጀመሩት በክብር እንግዳውን በደራሲ በገጣሚና በባለ ቅኔ ኃይሉ ገብረ ዮሃንስ የህይወት ታሪክና ዙርያና ያበረከቷቸውን የስነጽሁፍ ስራ በመዘርዘር ነበር። ደራሲው ዘመናት በማይሽረው ብዕራቸው የሚታወቁ እንደሆኑ ገልጸው በተለይም ”በረከተ መርገም” በተባለ የግጥም ስራቸው ለእስር ለእንግልት ለስደትና ለመንከራተት እንዳበቃቸው አስረድተዋል።

 

ደራሲ ገጣሚና ባለቅኔ ኃይሉ ገብረዮሐንስስለደራሲው በመጠኑ ለመግለጽና ማንነታቸውን ለማሳወቅ እንጂ ያላቸውን ታሪክና ስራ ለመዘርዘር ይህ አጭር ሰአት በቂ እንደማይሆን የገለጹት ወ/ሮ እመቤት ደራሲው በስደት አለም ለህዝብ ያበረከቷቸውን መጽሐፍቶች በዝርዝር አሰምተዋል። ከመጻህፍቶቹ መካከል ዜሮ ፊታውራሪ ፣ ቆርጠሃት ጣልልኝ፤ እናትክን ብሉልኝ የተባሉት ይገኙበታል።

 

ከዚህ አጭር ገለጻ በኋላ የተዘጋጀው የክብር ሸልማት ስጦታ የቦርዱ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ እንዳለ ወ/ስላሴ ለደራሲ ኃይሉ ገብረዮሃንስ አበርክተውል።ደራሲው በበኩላቸው በዚህ ስፍራ ከኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸው ጋር በመገኘት በዓሉን አብረው በማሳለፋቸው እንደተደሰቱ ገልጸው ስለተደረገላቸም ክብርና ስጦታ አመስግነዋል።

 

ቀጥሎም የኢትዮጵያ ድምጽ ሬድዮን በማቋቋም በማደራጀትና በበምራት እንዲሁም የዝግጅት አቅራቢ በመሆን ለአስራ ዘጠኝ ዓመታት ያህል የስራ አገልግሎት በመስጠት የቆዩት ጋዜጠኛ አህመድ አሊ ለሰሩት በጎ አገልግሎት የምስጋናና የክብር ሽልማት ከእለቱ የክብር እንግዳ ከደራሲ ኃይሉ ገብረዮሃንስ ተቀብለዋል።

 

ጋዜጠኛ አህመድ አሊ እሬድዮኑን በመምራት በቆዩበት ወቅት አያሌ ችግሮች እንደደረሰባቸው ተዘርዝሮ ያንን ሁሉ ፈታኝ ችግር በመቋቋም ከመደበኛ ስራቸው ጎን ለጎን በማስኬድ የሬድዮኑን ህልውና ሲአስጠብቁ እንደቆዩ በሽልማቱ ስነስርአት ላይ ተገልጿል። ጋዜጠኛ አህመድ በዛሬው ቀን የተደረግልኝ ሽልማት ፍጹም ያላሰብኩት ሲሆን ከፍተኛም ደስታ እንዲሰማኝ አድርጎኛል ብለዋል።

 

በበዓሉ ላይ ከተገኙ ታዳሚዎች መካከል ቂስ ፍስሃ ተስፋዬ የኢትዮጵያ ድምጽ ሬድዮ አገልግሎቱ ከፍ ያለ እንደሆነ ገልጸው እስካሁን ስለሰራው እየሰራም ስላለው ተግባር አመስግነዋል። ንግግራቸውንም በመቀጠል የኢትዮጵያ ድምጽ ሬድዮ በመኖሩ ልንሰባበብበት በመቻላችን እድለኞች ነን፣ በጠጨማሪ ከዚህ በላይ ሊአሰባስበን የሚችል የማህበረሰቡ ማህበር ቢኖር ደግሞ ይበልጥ ጠቃሚነት እንደሚኖረው አስረድተዋል።

 

በየዝግጅቱ ጣልቃ ድምጻውያኑ ተሾመ አሰግድ የዝና ነጋሽ እንዳለ ጌታነህና መረሱ ወንድማገኝ በሙዚቃ መሳሪያና በድምጽ የበዓሉን እንግዳ ሲያዝናኑ አርፍደዋል።በነጻነት አሰፋ የተመራም የህጻናት አበባየሁ ሆይ ተደምጧል።እንዲሁም በቹቹ ባህላዊ ውዝዋዜ ተጋባዙ እየተዝናና አርፍዶ የእለቱ ዝግጅት በዚሁ ተጠናቋል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ