በእስልምና ጉዳይ የመንግስት ጣልቃ ገብነት ማወዛገቡን ቀጥሏል
ትኩስ ወሬ ከሃገሬ - ሰኞመስከረም 7ቀን 2005 ዓ.ም
Ethiopia Zare (ሰኞ መስከረም 7 ቀን 2005 ዓ.ም. Sebtember 17, 2012)፦ የአህባሽን አስተምህሮ የሚቃወሙትንና መጅሊሱ እንዲለወጥ የሚጠይቁትን ሙስሊሞች ዓላማ ለማምከን እንደዚሁም ሕዝበ ሙስሊሙን በተለያየ አቋም ለመከፋፈል፤ኢሕአዴግ ከፍተኛ የካድሬ እንቅስቃሴ በማካሄድ ተግባር ተጠምዶአል።
ለራሱ ተጠሪነት ያላቸውን የሙስሊሙ ማህበረሰብ አባላትን አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በየክፍለ ከተማውና በየወረዳው ያደራጀው ኢሕአዴግ፤መስከረም 5 እና 6 ቀን 2005 ዓ.ም፡- “ሙስሊሞች የራሳቸውን ዑላማዎች ምክር ቤት ማቋቋም እንዲያስችላቸው መንግሥት ሁኔታዎችን አመቻችቷልና በየወረዳችሁ ጽ/ቤት እየተገኛችሁ እንድትመዘገቡ” ሲል ባወጣው መመሪያ መሠረት ጥቂት የማይባሉ ሙስሊሞች ከአገዛዙ ይመጣል ያሉትን ተጽዕኖ በመፍራት ወደየወረዳቸው መመዝገቢያ ጣቢያ በመሄድ ተመዝግበዋል። ምዝገባውን ተከትሎ በተመዝጋቢዎቹና ባልተመዘገቡት ሙስሊሞች መካከል የሃሳብና የአቋም ልዩነት መፈጠሩም ታውቋል።
ያልተመዘገቡት ሙስሊሞች፡- “የታሰሩት ወኪሎቻችን እስካልተፈቱ ድረስ መንግሥት በዕምነታችን ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ሊያሳድር የሚችለውን ማንኛውንም ተጽዕኖ ለመቀበል ፈቃደኞች አይደለንም! ከሁሉም ነገር በፊት የታሰሩት ይፈቱ፣ የታሰሩት ሳይፈቱ የሚደረግ ማናቸውም ዓይነት የመንግሥት እጅ ያለበት ስብሰባና የዑላማዎችን ም/ቤት አባለት ለመምረጥ የሚደረግ እንቅስቃሴ የፖለቲካ ካድሬዎችን መጠራራት እንጂ የሙስሊሙ ጥያቄ እየተመለሰ መሆኑን አያመለክትም” እያሉ ናቸው።
በየወረዳው ከተመዘገቡት መካከል በጣም ጥቂቶቹና ባስተባባሪነት ተግባር ላይ የሚገኙት አፍቃሪ ኢሕአዴጎች ደግሞ፡-“የታሰሩት ሕገ-ወጦችና ፀረ-ሕገ መንግሥት ናቸው፣የሙስሊሙንም ማህበረሰብ አይወክሉም…” በማለት ቅዋሜያቸውን በለውጥ ፈላጊዎቹ ላይ ከማሰማት አልተቆጠቡም።
ራሳቸውን በታዛቢነት ሥፍራ ያስቀመጡ ወገኖች በበኩላቸው፡- “ከኢሕአዴግ ጋር ተሰልፈው የዑላማ ም/ቤት አባላትን አንመርጣለን፣ታሳሪዎችንና ተግባረቸውን እናወግዛለን በማለት ድምጻቸውን የሚያሰሙት ሙስሊሞች ዕምነታቸውን በምንዳ የለወጡና ከእስልምና ሃይማኖት ይልቅ ከኢሕአዴግ አባልነት ሊገኝ የሚችለውን ፖለቲካዊ ጥቅም የመረጡ ተላሎችና ህይወት የተሳከረችባቸው ናቸው፣ስለ እስልምና እምነትም የጠለቀ ግንዛቤ የሌላቸው በመሆኑ የዑላማዎችን መ/ቤት ለማቋቋም ብቁዎች አይደሉም” ሲሉ ነቅፈዋል፡፡ አያይዘውም፡- “የሙስሊሞች የዕምነታቸው ጉዳይ ነጻና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ፣ያለመንግሥትም ጣልቃ ገብነት ለራሳቸው ለባለጉዳዮቹ መተው እንዳለበትና በኢትዮጵያ ሰፍኖ የኖረው የተለያዩ ዓማንያን በወንድማማችነት ተግባብቶ የመኖር ባሕል የሚደረጅበት ሁኔታ ጎልብቶ፣ልዩነትን መሠረት የሚያደርገው ፖለቲካዊ ጣልቃ-ገብነትም የከፋፋይነት ሥለቱ መዶልደም አለበት” በማለት መክረዋል።
ባለፈው ሐሙስ እና ዓርብ መስከረም 3 እና 4 ቀን 2005 ዓ.ም በፌደራሉ የመጀመሪያ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ችሎት እንዲቀረቡ የተደረጉት የለውጥ ፈላጊው ሙስሊም ማህበረሰብ ወኪሎች ለጥቅምት 1እና2 ቀን 2005 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ የተያዘላቸው መሆኑ ይታወሳል።



