የሙስሊሞች ተቃውሞና እስራት ቀጥሏል
በሞባይላቸው መልእክት የተላላኩ እየታደኑ ነው
Ethiopia Zare ቅዳሜ መስከረም 15 ቀን 2005 ዓ.ም. Sebtember 22, 2012)፦ የመለስ ዜናዊ ሞትና የቀብር ሥርዓታቸው አፈጻጸም ጉዳይ ረገብ አድርጎት የቆየው የሙስሊሞቹ የመብታችን ይከበር ጥያቄ ዓርብ መስከረም 11 ቀን 2005 ዓ፣ም በታላቁ አንዋር መስጂድ ሲቀጥል በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሙስሊሞች “መሪዎቻችን ይፈቱ! ያታሰሩት ሳይፈቱ የዑላማዎች ምርጫ አይካሄድም! ምርጫው የሚካሄደውም በመስጂድ ብቻ መሆን አለበት!መንግሥት ከጣልቃ ገብነት ተግባሩ ያታቀብ!...” የሚሉና ሌሎች የመብት ማስከበሪያ ጥያቄ ድምፆችን “አላህ ወ አክበር!” ከሚለው ተክቢራ ጋር ደጋግመው አሰምተዋል፡፡
የዕለቱን “በመስጂድ ተቃውሞ አታሰሙ” የሚለውን የአንድ ሃይማኖት አባት ምክር ወይም “ሁጥባ” ተከትሎ የተሰማው የቅዋሜ ድምፅ ነጭ ማሃረብን በማውለብለብ የታገዘ ነበር፡፡ መስከረም 11 ቀን በጁምዓ ሰዓት አንዋር መስጂድንና አካባቢውን ያጠለቀለቁት ሙስሊሞች የታላቁን አንዋር መስጂድ ኢማም ሃጂ ጠሃ ሃሩንን ሲያወግዙም ተደምጠዋል፡፡ በአካባቢው ሠፍሮ የቆየውንና ከመስጂድ ውጭ ባለው ሥፍራ ምዕመናም እንዳይሰባሰቡ ለማድረግ ፍላጎት የነበረውን ነገር ግን ሁኔታውን በማጤን ከድርጊቱ የታቀበውን የፌደራል አድማ በታኝ ኃይል ከምንም ሳይቆጥሩ ሰላማዊ ተቃውሞአቸውን ያሰሙት ሙሰሊሞች፤በዕለቱ ሳይቋረጥ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ወደየመጡበት ተመልሰዋል፡፡
ሙስሊሞቹ በአንዋር መስጂድ የተሰባሰቡት ቀደም ሲል በተንቀሳቃሽ ስልክ፣በፌስ ቡክና በአካል ሲያደርጉት በቆዩት “ተሰባስበን ድምጻችንን እናሰማ…” ጥሪ መሰረት መሆኑን ለማወቅ የተቻለ ሲሆን፤ፖሊስም በተንቀሳቃሽ ወይም በሞባይል ስልክ “ጥሪ ሲያስተላልፉ ነበር…” ያላቸውንና በዚህ ረገድ የጠረጠራቸውን ሙስሊሞች ይዞ ማሰሩን ለፖሊስ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ለዜና ሰዎች አስረድተዋል፡፡ እነዚሁ ምንጮች እንዳስረዱት ከሆነ ድምፃችንን ለማሰማት እንሰባሰብ… የሚል መልዕክት በሞባይላቸው ላይ የተገኘ በርካታ ወጣት ሙስሊሞች ያለ ፆታ ልዩነት ለእስር ተዳርገዋል፡፡ወይም ሞባይላቸውን “ለምርመራ ይፈለጋል” በሚል ምክንያት እንዲያስረክቡ ከተደረጉ በኋላ ተይዘው ተለቀዋል፡፡



