በአዲስ አበባና ድሬደዋ የውሃና መብራት ችግር ተባብሷል
የሃገር ወሬ (ታላቅ ሰው ምንአለ ከአዲስ አበባ)
ለመብራት ችግር ምክንያት የሆነውን ትራንስፎርመር ለመተካት 30 ሚሊየን ብር ተጠየቀ!
ትራንስፎርመሩን እንዴትና በማን እንደተሰረቀ እስካሁን አልተገለጸም!
Ethiopia Zare (ረቡዕ ጥቅምት 7 ቀን 2005 ዓ.ም. October 17, 2012)፦ በአዲስ አበባ በርካታ አካባቢዎች በተለይም በቂርቆስ ክ/ከተማ፣ በየካ ክ/ከተማ፣ በጉለሌ ክ/ከተማ፣ በኮልፌ ቀራንዮና በአዲስ ከተማ ክ/ተማዎች ከፍተኛ የውሃ ዕጥረት ተስተውሏል።
ይህ የሆነውም የክረምቱ ወር ዝናብ መስከረም 18 ቀን በመሃል ሃገር መቆሙን ተከትሎ ነው። በየካ ክ/ከተማ፣ ፈረንሳይ ለጋሲዮን ልዩ ስሙ እየሱስ ማዞሪያ፣ ጉራራና ብረት ድልድይ በተባሉ መንደሮች የመጠጥውሃ ችግር መፈጠር ከጀመረ ከ 5 እስከ 6 ቀናት ያስቆጠረ ሲሆን ፊትን እስከመታጠብ ብርቅ እየሆነ መምጣት ድረስ የችግሩ አድማስ ወሰኑን እያሰፋ ነው።
በኮተቤ የውሃው ችግር የተባባሰ ሲሆን የመጠጥ ውሃ ዕጥረቱ ወይም ከናካቴው የመጥፋት አዝማሚያው ከ10 ወደ 15 ቀን መሸጋገሩን የጥቅምት 3 ቀን 2005 ዓ.ም ማለዳ መረጃ ቢያመለክትም የአካባቢው ነዋሪዎች ችግሩ ዘለቄታዊ መፍትሄ የማይፈለገለት ከሆነ ለከፍተኛ የጤና ችግር መጋለጣችን የማይቀር ነው ሲሉ ስጋታቸውን በመገለጽ ላይ ናቸው።
በጉለሌ ክ/ከተማ በተለምዶ ሽሮ ሜዳ ተብሎ በሚታወቀው የመዲና አዲስ አባባ ነባር ሠፈርና በአቅራቢያው ይስተዋል የነበረው የውሃ ችግርም ከነበረበት በከፋ ሁኔታ ቀጥሏል።
በአራት ኪሎ አርበኞች ሕንፃ ሥር የሚገኘው የአባት አርበኞች ክበብ የውሃ አገልግሎት የሌለው መሆኑን ዘጋቢያችን መስከረም 30 ቀን ከቀትር በኋላ በቦታው ተገኝቶ ሁኔታውን ያረጋገጠ ሲሆን በክበቡ የመጠጥ ውሃ ማግኘት የማይቻል መሆኑንና ካለው የውሃ ችግር ጽናት የተነሳም የመጸዳጃ ቤቱ መጥፎ ጠረን ሻይ ቡና አዘውም ሆነ ምግብ ለመቅመስ የሚቀመጡትን ሰዎች እንደሚረብሽና ለፈጣን የጤና ችግር እንደሚዳርግም ነው መታዘብ የቻለው። በፓራላማው መቀመጫ ፊት ለፊት እንደዚህ ዓይነት ጉልህ ችግር መፈጠሩ ግርምት የፈጠረበት መሆኑንም ግልጽ አድርጓል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በድሬ-ዳዋ፣ በሐረር፣ በሂርና፣ በአሰበ ተፈሪና በሌሎች የኢትዮጵያ ምስራቃዊ ከተሞች የመጠጥ ውሃ ዕጥረቱ በአስደንጋጭ ሁኔታ ተባብሶ መቀጠሉን ጥቅምት ሁለት ቀን 2005 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ ከወደ ሥፍራው የደረሰን መረጃ አመልክቷል። መረጃው እንዳመለከተው ከሆነ በከተሞቹ የተከሰተው የውሃ ችግር ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የመብራት መቋረጥና የነዳጅ ዕጦትም ነው።
የመብራት ወይም የኤሌትሪክ መቋረጡ ችግር ከተከሰተ ከአራት ቀናት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን ይኸው ችግር ከአሰበ ተፈሪ እስከ ጅጅጋ ድረስ ያለውን የሃገሪቱን ምስራቃዊ ግዛት ያካለለ ነው። ነዳጅም፣ መብራትም፣ አሳሳቢውና ፋታ የማይሰጠው የውሃ ችግርም በገጠማቸው የምስራቅ ኢትዮጵያ ከተሞች ነዋሪው ሕዝብ መንፈሱ የተረበሸ ቢሆንም የችግሩን ምንጭ መግለጽ ያልወደደው የአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ መንግስት እስካሁን ለተደራራቢው ችግር መፍትሄ ለመፈለግ በመሯሯጥ ላይ መሆኑን የመንግሥቱ ቅርብ ሰዎች በመንግስት መገናኛዎች በመናገር ላይ ሲሆኑ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ባሰራጨው ወሬ መብራት ሊጠፋ የቻለው የትራንስፎርመር ስርቆት በመፈጸሙ ነው ከማለቱም በላይ በኤሌክትሪክ መስሪያ ቤቱ ይህንኑ መሳሪያ ለመተካት 30 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልገው ይፋ ተደርጓል። ነገር ግን አስራ አራት የሃገሪቱን ከተሞች ጭር ያረገውን የኤሌትሪክ እጥረት ያስከተለውን ትራንስፎርመር ማን ሰረቀው? ለሚለው መልስ የሚሰጥ ወገን አልተገኘም።



