የዛሬ 87 አመት የወጣ የአውዳመት ዜና!
Ethiopia Zare (ማክሰኞ ታህሳስ 23 ቀን 2005 ዓ.ም. January 1, 2013)፦ የዛሬ 87 አመት ብርሃንና ሰላም የተባለ ጋዜጣ አውዳመትን አስመልክቶ ያወጣውን አንድ ዜና ፈገግ ቢያሰኝዎ በሚል አቅርበንልዎታል። መልካም የፈረንጆች አዲስ አመት እንዲሆንልዎ እንመኛለን።
የዛሬ 87 አመት የወጣ የአውዳመት ዜና!
ከመጠጥ የሚገኝ ጉዳት
ታህሳስ 29 የክርስቶስ ልደት እለት አቶ ቢራቱ የሚባል እንጦጦ ራጉኤል ገዳም ውስጥ የነበረ ሰው በልደት በዓል ቀን አራዳ አረቄ ሲጠጣ ውሎ ወደ ማታ በፈረስ ተቀምጦ ወደ ቤቱ ሲወጣ ራጉኤል አፋፍ በደረሰ ጊዜ ሰውነቱ በመጠጥ ዝሏልና ተኮርቻ ተገልብጦ ወደቀ፤ እነሳለሁ መስሎት እየተንከተከተ /እየሳቀ/ አረሀ ላረሀ ሲንደባለል አሽከሩ እንደ እሱ አልባሰበትም ነበርና ከቤቱ ሄዶ ሰዎች ይዞ እስቲመጣ ድረስ እሱ አረፋ ደፍቆ ሆዱ ተነፍቶ ሞቶ ተገኘ። ብዙ ሞኞች ጋኔን ገደለው እያሉ ያወራሉ ግን ካረቄ የበለጠ ጋኔን እንደሌለ ባያውቁ ነው።
ብርሃንና ሰላም ጋዜጣ
ጥር 6 ቀን 1918 ዓ.ም



