ዶ/ር ያቆብ ኃ/ማርያም ለፖሊስ ቃላቸውን ሰጥተው በዋስ ተለቀቁ
ከሳሻቸው አቶ አየለ ጫሚሶ ነው
Ethiopia Zare (ማክሰኞ ሰኔ 10 ቀን 2000 ዓ.ም. June 17 2008)፦ ዶ/ር ያቆብ ኃይለማርያም “አውራምባ ታይምስ” ከተሰኘው በሀገር ውስጥ ከሚታተም ጋዜጣ ጋር ያደረጉትን ቃለምልልስ ተንተርሶ በአቶ አየለ ጫሚሶ በተመሰረተባቸው ክስ ትናንት አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተጠርተው ቃላቸውን ከሰጡ በኋላ በዋስ ተለቅቀዋል።
ትናንት ከሰዓት በኋላ ስምንት ሰዓት ላይ ፖሊስ ጣቢያው ቀርበው ቃላቸውን የሰጡበት ክስ በአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ላይ በሰጡት ቃለምልልስ ላይ “የቅንጅትን ስም ለማንም መንገደኛ ተሰጥቷል” በማለታቸው እንደሆነ ታውቋል።
ዶ/ር ያቆብ ለፖሊስ ቃላቸውን ከሰጡ በኋላ የሁለት ሺህ ብር ዋስ ጠርተው ተፈትተዋል። ዓርብ ሚያዝያ 3 ቀን 2000 ዓ.ም. ዶ/ር ያቆብ እና የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ዳዊት ከበደ መከሰሳቸውን መዘገባችን አይዘነጋም።



