ሰዓሊ ያሬድ ንጉሱ የሳለው የኦባማ ምስል (ፖርትሬት) ለእይታ ቀረበ
የአሜሪካ ካውንስል ጄኔራል የሆኑት ካውንስሌት አን ካላጋን መርቀውታል
![]() |
| የአሜሪካ ካውንስል ጄኔራል አን ካላጋን እና ሰአሊ ያሬድ ንጉሱ |
Ethiopia Zare (ሰኞ ጥር 13 ቀን 2005 ዓ.ም. January 21, 2012)፦ ኢትዮጵያዊው ሰአሊ ያሬድ ንጉሱ የመጀመሪያውን ጥቁር አሜሪካዊ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን ፖርትሬት ለሁለተኛ ጊዜ ቃለ መሀላ ከፈጸሙበት ከዛሬ እለት ጀምሮ በቫንኩቨር ካናዳ በሚገኘው የአሜሪካ ኢምባሲ ለሶስት ሳምንታት ለእይታ መቅረቡ ታወቀ። በቫንኩቨር ካናዳ የአሜሪካ ካውንስል ጄኔራል የሆኑት ወ/ት አን ካላጋን በምረቃው ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።
ይሄው 86 ኢንች በ109 ኢንች ወይንም 2ሜትር ከ20 በ 2ሜትር ከ80 ትልቀት ያለው ፓርትሬት በስድስት ካንቫሶች ተወጥሮ የተሰራ ሲሆን ስያሜውም በእንግሊዝኛ ‘ከለርፉል ቪክትሪ’ (colorfull victory) የሚል ሲሆን በአማርኛ የተሰጠው ስምም የ’ድል ተስፋ’ እንደሆነ ለማወቅ ችለናል።
ያሬድ ለስእሉ ጅማሬ የሆነው ‘ይህ ጥቁር የሆነ ሰው ብቻ ሳይሆን እንደ ማንኛውም ሰው ከማህበረሰቡ የወጣ አቶ ኦባማ የተባለ ግለሰብ ህልሙን እውን ለማድረግ ፈተናዎች ቢበዙበትም ፈተናዎቹን ሁሉ አልፎ ለዚህ መብቃቱ በየትኛውም የአለም ክፍል ለሚገኙ ወጣቶች ትልቅ የተስፋ ምሳሌ መሆናቸው እንደሆነ በተለይ ለኢትዮጵያ ዛሬ ገልጿል።
አስከትሎም “ማንም ሰው ተስፋ ሳይቆርጥ የሚያምንበትን ከግብ ለማድረስ ከተጓዘ ህልሙን ባለቀለም ማድረግ እንደማይከብደው በቀላሉ ያሳዬ መሪ ናቸው” ሲል ለፕሬዝዳንቱ ያለውን አድናቆት ገልጿል።
ሰአሊ ያሬድ በካናዳ ውስጥ በከፍተኛ ፍጥነት ዝናቸው ከናኙ ሰአሊያን አንዱ ሲሆን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ የጥበብ ምድር ከሆነችው ፈረንሳይ የስእል ጥበብ ትምህርት የተከታተለ ሲሆን በአሁኑ ሰአት መቀመጫውን ቫንኩቨር ካናዳ በማድረግ በርካታ ስራዎቹን ለህዝብ እይታ በማብቃት ላይ ይገኛል።
የፕሬዝዳንት ኦባማን ምስል በስድስት ትላልቅ ካንቫሶች ላይ ተስለው ለቀጣዮቹ ሶስት ሳምንታት በኢምባሲው ከቆዩ በኋላ የጥቁር ታጋዮች መታሰሚያ የሆነውን ፌብርዋሪ ወርን ሙሉ በአለማችን አንቱ ከተባሉት ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ በሆነው ሳይመን ፍሬዘር ዩኒቨሪሲቲ ውስጥ ለእይታ እንደሚቀርብ ለመረዳት ተችሏል።
የያሬድ ንጉሱን ስራዎች ለመመልከት ይህንን ይጫኑ።




