33ቱ ፓርቲዎች ኢህአዴግን አስጠነቀቁ
(ፍኖተ ነፃነት ጥር 27 ቀን 2005 ዓ.ም.) 33ቱ ፓርቲዎች “ኢህአዴግ ስለ አካባቢ ምርጫ የሰጠው መግለጫ የጥያቄዎቻችንን ትክክለኛነትና አግላይ አቋሙን ያረጋገጠበት ነው” በሚል ርዕስ መግለጫ አወጡ። ኢህአዴግን አቋሙን እንዲያስተካክልም አስጠነቅቀዋል።
የኢህአዴግ ጽ/ቤት ኃላፊና የምርጫ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ የአቶ ሬድዋን መግለጫ ኢህአዴግ ዛሬም በአገራዊና ህዝባዊ ጉዳዮች ላይ ለሚነሱ ጥያቄዎች በሙሉ ወሳኝም፣ ባለመፍትሔም እኔ ብቻ ነኝ ከሚል የእብሪት ስሜት አለመላቀቁንና ኃላፊነት በጎደለው ጭፍን ጥላቻ እየተነዳ መሆኑን ያመለክታል ያለው የፓርቲዎቹ መግለጫ፤ “ይህ አካሄድ ለማንም የማይጠቅም ከመሆኑም በላይ ብዙ ርቀት ሊያስኬደው እንደማይችል በድጋሚ ሊገለጽ ብቻ ሳይሆን በህዝባዊ ኃይል ሊገታ የሚገባው መሆኑን እንረዳለን” በሚል አሳስቧል።
ፓርቲዎቹ መግለጫቸው ያቀረቧቸው ጥያቄዎች ቀላል እንደሆኑ አስገንዝቧል። ጥያቄያቸው ሲጠቃለል መንግስትና ኢህአዴግ ይለያዩ፣ የመገናኛ ብዙሀን ፍትሀዊ አጠቃቀም ይኑር፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት ይከበር፣ ምርጫ ቦርድ ከገዥው ፓርቲ ተጽዕኖ ተላቅቆ በነፃነት ይደራጅ! የሕግ የበላይነት ይረጋገጥ፣ በገዥው ፓርቲ አማካይነት ለአፈና የወጡ ሕጎች ይከለሱ/ይሻሩ፣ በድምሩ የዜጎች ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ተከብረው የህዝብ የሥልጣን ባለቤትነት ይረጋገጥ ዘንድ የምርጫ ሜዳው ይስተካከል የሚሉ ናቸው በማለት የጥያቄዎቹን ዘርዝረዋል።
33ቱ የአዳማ ፔቲሽን ፈራሚ ፓርቲዎች ጥር 26 ቀን 2005 ዓ.ም. ህዝባዊ ስብሰባ ለማድረግ ቢያቅዱም የመሰብሰቢያ አዳራሾችን እንዳያገኙ በመንግስት ጫና እየተደረገባቸው በመሆኑ ስብሰባውን ለማራዘም መገደዳቸው ታውቋል።



