በጅሃዳዊ ሐረካታ ፊልም ላይ ከ33ቱ ፔቲሽን ፈራሚዎች የተሰጠ መግለጫ
Ethiopia Zare (ሐሙስ የካቲት 7 ቀን 2005 ዓ.ም. February 14, 2013)፦ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በተከታታይ ያሳየውን ”ጅሃዳዊ ሐረካት” የተሰኘ ፊልም አስመልክቶ፤ ሰላሳ ሦስቱ ፔቲሽን ፈራሚዎች ባወጡት መግለጫ ”ለዘመናት በፍቅርና መከባበር የኖረን ህዝብ በደረቅ ፕሮፓጋንዳ መነጣጠልና መከፋፈልም ሆነ የመብት ጥያቄውን ማዳፈን አይቻልም!” በማለት በፊልሙ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ገልጸዋል።
መግለጫው ”የፊልሙ ዓላማ የህዝብን የዘመናት አብሮነት መሸርሸርና የመብት ጥያቄ የሚያነሳን ከሽብርተኝነትና ጦርነት ጋር በማያያዝ ህዝብን ለማሸማቀቅ ሆኖ በውጤቱም ህዝብ በአገሩ ላይ ያለውን የባለቤትነትና ኃላፊነት ስሜት በመናድ አንገት ማስደፋትና መብት ጠያቂዎችን በመነጣጠልና በመከፋፈል ጥያቄዎችን ማዳፈንና ማፈን ነው” በማለት የፊልሙን ለህዝብ መተላለፍ ኮንኖታል።
ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ባለውና በእስር ላይ በሚገኙት የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ላይ የሚያነጣጥረው ይኸው ፊልም በተደጋጋሚ መታየቱን ጨምሮ አውግዞአል።
መንግሥት ትናንት የኮሚቴ አባላቱን ውክልና ተቀብሎ ሲያወያይ እንዳልነበረ ውይይቱ ያለውጤት ሲቋረጥ ”አሸባሪ” በሚል መክሰሱ የሚያሳየው ኢህአዴግ በባህሪው የተለየ ሃሳብና ጥያቄ ካላቸው ወገኖች ጋር ተወያይቶ መፍትሔ ለማምጣት ድፍረትና የሞራል መሠረት የሌለው፣ ሕግን ለሀገርና ለህዝብ ደህንነት መጠበቂያ ሳይሆን ለራሱ ለፓርቲው ጠባብ ፍላጎትና ዓላማ ማስፈጸሚያ፤ እንዲሁም የማይመቹትን ያላግባብ ለመጉዳት የሚጠቀም መሆኑ ነው ሲል መግለጫው የኢህአዴግን ድርጊት ይኮንናል።
33ቱ ፔቲሽን ፈራሚዎች ያወጡትን ሙሉ መግለጫ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!



