አቶ ፋንታሁን አሰፋ Fantahun AssefaEthiopia Zare(እሁድ የካቲት 17 ቀን 2005 ዓ.ም. February 23, 2013)፦ በስዊድን የሚገኘው የኢትዮጵያ ስደተኞች ማኅበር የኢትዮጵያን ጉዳይ ከሚከታተሉ የኢሚግሬሽን ተወካዮች ጋር ፌብሪዋሪ 6 ቀን 2013 ዓ.ም ውይይት አደረገ። ይህንኑም ጉዳይ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ እስር ቤት ከርመው የተፈቱት ጋዜጠኞች ማርቲን ሼቢ እና ዮሃን ፐርሾን ለኢሚግሬሽን ባለስልጣናት እንዳስረዱ አቶ ፋንታሁን ገልጸዋል።

 

በዚህ ውይይት ላይ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አባላት የተገኙ ሲሆን፣ የማኅበሩ ሰብሳቢ አቶ ፋንታሁን አሰፋ ስለውይይቱ ለኢትዮጵያ ዛሬ ሲያስረዱ፤ ውይይቱ በስዊድን የሚገኙ ፈቃድ ያላገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ፈቃድ እንዲሰጣቸው ለመጠየቅና እየተባባሰ የመጣውንም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር ለማስረዳት እንደሆነ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት አገር ቤት ያሉትን ዜጎች ላይ ብቻ ሳይሆን የውጪውንም ለመቆጣጠርና ለማጥቃት እንደተነሳ በመጠቆም፤ የኢትዮጵያ ስደተኞች ጉዳይ ልዩ ግንዛቤ አግኝቶ የፍቃድ ጥያቄያቸው ተገቢ መልስ እንዲያገኝ ለተወካዮቹ ማስረዳታቸውን አቶ ፋንታሁን ገልጸዋል።

ከተወካዮቹ የተገኘው መልስ ምን እንደሆን ለጠየቅናቸው ጥያቄ መልስ ሲሰጡ፤ እኛ የተናገርነውን በሙሉ የነሱን ሃሳብ አክለው ለሚመለከተው ክፍል እንደሚያቀርቡ ጉዳዩንም እንደሚከታተሉ የገለጹላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ አጋጣሚ የስዊድን የኢትዮጵያውያን ስደተኞች ማኅበር መቼ እንደተመሰረተ፣ ዓላማው ምን እንደሆነ፣ እስካሁን ምን የስራ አገልግሎት እንዳበረከተ፣ ለወደፊትስ ያለው የሥራ ዕቅድ ምን እንደሆነ ለጠየቅነው ጥያቄ የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ አቶ ሚሊዮን ብሩና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ግሩም ጌታ ዘላለም በየተራ መልስ ሰጥተዋል።

ማኅበሩ በ2009 ዓ.ም. እንደተመሰረተ ዓላማውም በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ የነፃነት ረገጣና የፍርድ መጓደል ለውጨው የዓለም ክፍል ማሳወቅ፣ ስደተኛው በስደት ሀገር ያለውን መብት እንዲረዳ ማገዝ፣ ማማከር፣ የስዊድን የስደተኛ ጉዳይ መስሪያ ቤት ስለኢትዮጵያ ስደተኞች ያለውን አመለካከት ማስቀየር፣ መሆኑን ገልጸዋል።

ማኅበሩ እስካሁን ምን አገልግሎት እንዳበረከተ ሲያስረዱ ደግሞ፤ ብቻውን ጉዳዩን ይዞ የሚነጋገረው ስደተኛ አንድ በሚያደርገው ነገር እንዲመክር፣ መንግስት የሚያቆምላቸው ጠበቃ ሲነሳ ለአባላት ሌላ ጠበቃ በማቆም ጉዳያቸው እንደገና እንዲታይ ለመርዳት፣ እንዲሁም በአድራሻ እጦት የሚቸገሩ ስደተኞች የማኅበሩን የፖስታ አድራሻ እንዲጠቀሙ ለማድረግ ችለናል ብለዋል።

በተጨማሪም አወዛጋቢ በሆነ ምክንያት የታሰሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እንዲፈቱ፤ ወደ ሃገር ቤት አላግባብ የተላከም ስደተኛ ከሚመለከተው ክፍል ጋር በመነጋገር እንዲመለስ አድርገናል ብለዋል። ስለማኅበሩ የወደፊት እቅድና ቀጣይ ስራ ደግሞ አሁን የጀመርነው ስራዎችን ከግብ ማድረስ፣ የስደተኛ መስሪያ ቤት ሙሉ ለሙሉ ስለኢትዮጵያ ስደተኞች ያለውን አመለካከት እንዲቀይር፣ ስደተኛው ማወቅ የሚገባውን ዓለም አቀፍ የስደተኛ መብት እንዲያውቅ ማድረግ ያለበትን ሃገርም ሕግ አክብሮ መኖርና መስራት እንዲችል መቅረጽ ... ዋናው ተግባራችን ነው ብለዋል።

አንድነት ኃይል መሆኑን የገለጹት ወ/ሮ ሙሉ አበበ በበኩላቸው ማኅበሩ ባሁን ጊዜ 164 አባላት ያሉት መሆኑን ጠቅሰው ማኅበሩ እስካሁን የተሰራውም ስራ ቀላል ባይሆንም ይበልጥ ተደራጅቶና የአበላቱን ቁጥር አስፍቶ ቢንቀሳቀስ ደግሞ ይበልጥ ተሰሚነት እንደሚኖረው በመግለጽ ፍቃድ የሌላቸው ስደተኞች በማኅበሩ እንዲታቀፉ ጥሪ አድርገዋል። ወ/ሮ ሙሉ ማኅበሩን በገንዘብ ያዥነት የሚያገለግሉ ናቸው።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ