የጋዜጠኞቹ እስክንድር ነጋ፣ ርዕዮት አለሙና ውብሸት ታዬ ምስል 33ሺህ ዶላር በጨረታ ተወስዷል

Ethiopia Zare (ሰኞ ሚያዚያ 14ቀን 2005 ዓ.ም. April 22, 2013)፦ ትላንት ምሽት በሲያትል ከተማ የኢሳትን ሶስተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ አርቲስትና የሰብአዊ መብት ተሟጋች የሆነው ታማኝ በየነ እና አቶ መንሱር ኑር በክብር እንግድነት የተገኙበት የገንዘብ ማሰባሰቢያ ምሽት ላይ 50ሺህ የአሜሪካን ዶላር መሰብሰቡ ታወቀ።

ትላንት እሁድ ሚያዚያ 21 ቀን 2013 ዓ.ም በሲያትል በተደረገው በዚሁ የኢሳት ምሽት ላይ ከ600 ሰው በላይ መገኘቱ ይፋ ተደረገ ሲሆን ከቅንጅት ጊዜ ወዲህ እንዲህ አይነት ታላቅ ተሳትፎ በከተማዋ ሲደረግ የመጀመሪያ መሆኑን ለመረዳት ችለናል።

በተለይ ኢሳትን በገንዘብና በሞራል ለማጠናከር በተለያዩ አለማት በመዘዋወርና አዳዲስ የቪድዮ መረጃዎችን በመያዝ ለታዳሚዎች በማቅረብ የሚታወቀው ታማኝ በየነ የተለያዩ ድንቅ ስራዎቹን ለሲያትል ነዋሪዎች ያቀረበ ሲሆን በስፍራው በተጋባዥነት የተገኙት አቶ መንሱር ኑርም በተለይ ከአመት በላይ የዘለቀውን የሙስሊሙን ማህበረሰብ ሰላማዊ እንቅስቃሴ በማስመልከት ንግግር ማድረጋቸው ታውቋል።

በሲያትል የኢሳት ድጋፍ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሙሉነህ ዩሀንስ ለኢትዮጵያ ዛሬ እንደገለጸው ሲያትል የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ ጊዜያት በሀገራችን ውስጥ ለሚፈጠሩ ሀገራዊ ችግሮች ፈጥኖ በመድረስ የሚታወቅ መሆኑን በመግለጽ በትላንትናው እለት በተደረገው የገንዘብ ማሰባሰቢያ ምሽት በርካታ የኢሳት ደጋፊዎች ያሳዩት ተሳትፎ ከመቸውም የተለየ ሆኖ ማግኘቱን ገልጿል።

በዚሁ የኢሳት ምሽት ላይ ከቫንኩቨር ካናዳና ከፖርትላንድ አካባቢ የተገኑ ኢትዮጵያዊያን ታዳሚዎች ከመገኘታቸውም በላይ በቫንኩቨር የሚተላለፉት መለከት የኢትዮጵያ ራዲዮና በኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህ ጠፍቷል በማለት በዳውሮ ከተማ ራሱን ባቃጠለው ወጣት ኢትዮጵያዊ ስም በተሰየመው የኔሰው ራዲዮ አማካኝነት በአጭር ጊዜ በተደረገ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ከአድማጮች የተሰበሰበ 1000ሺህ ዶላር በአርቲስት ታማኝ በኩል ለኢሳት ገቢ እንዲደረግ መላኩ ተገልጿል።

የእውቁ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፤ የአምደኛና መምህርት የሆነችው ርእዮት አለሙ እና የጋዜጠኛ ውብሸት ታዬን ምስል የያዘ ፎቶ ለጨረታ ቀርቦ 33ሺህ ዶላር በጨረታ የተወሰደ መሆኑንም ከስፍራው ለማቀቅ ተችሏል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!