በ17 ዓመቷ ራሷን ያጠፋችው ወጣት ቤተሰቦች ልምድ ያካፍላሉ!

“በእኔ ቤተሰብ የደረሰ ልብ የሚሰብር ሀዘን በሌሎች ወገኖቼ ላይ ደርሶ ማየት አልፈልግም” (የኤደን ወላጅ አባት)

‘ልጄን እንደ ንግስት ነበር ያሳደኳት፤ የዚህ ሀገር ልጅ ምኑም አይታወቅም”  የኤደን እናት ወ/ሮ በለጡ

ደራሲ ሐምራዊት ተስፋ በውይይቱ ላይ ትናገራለች!

የአማንዳ ቶድ ወላጅ እናት በውይይቱ ተካፋይ ናቸው!

Ethiopia Zare (ሰኞ ግንቦት 5ቀን 2005 .. May 13, 2012)ባለፈው መስከረም 24 ቀን 2012 ዓ.ም በቫንኩቨር ካናዳ ህይወቷን ያጣችው የ17 ዓመት ታዳጊ ወጣት ኤደን ዘውዱ ቤተሰቦች በራሳቸው ቤተሰብ የደረሰ ሀዘን በሌሎች ወገኖች ላይ እንዳይደርስ ለማንቃት ተግተው እንደሚሰሩ አስታወቁ። በኖርዝ አሜሪካ ልጆችን ለማሳደግ የሚያስችሉ ጥናቶችን ያካተተ መጽሐፍ የጻፉት ደራሲ ሐምራዊት ተስፋም ተጋባዥ መሆናቸው ታውቋል።

 

ወጣት ልጃቸው ኤደን ተዘራ ባለፈው የኢትዮጵያዊያን አዲስ አመት ካለፈ ከሳምንት በኋላ በቫንኩቨር ከተማ  በርናቢ በሚባለው አካባቢ በሚገኝው ዲር ሌክ ሐይቅ ውስጥ ራሷን ያጠፋችው ታዳጊ ወጣት ኤደን ዘውዱ እልፈት በኋላ ጥልቅ ሐዘን ውስጥ የሰነበቱት ቤተሰቦቿ ፕሮጄክት ኤደን የተሰኘ መርሃግብር አዘጋጅተው እንቅስቃሴ መጀመራቸው ታወቀ።

 

የኤደን ቤተሰቦች በተለይ እናትና አባቷ ወ/ሮ በለጡ ተዘራ እና አቶ ዘውዱ ጎሳ በሰሜን አሜሪካ ልጆችን ማሳደግ ምን ያህል ፈተና የበዛበት መሆኑንና በርካታ ጥንቃቄ ሊወሰድባቸው ጉዳዮችን ለመጠቆም የቤተሰባቸውን ጥልቅ ሀዘን የተሞላበት ተሞክሮ ለሌሎች ለማካፈልና የወጣቶችን ያለእድሜ መቀጨት ለመቀነስ የሚያስችል አላማ በማንገብ ማህበረሰቡን ለማስተማር ቆርተው መነሳታቸውን በተለይ ለኢትዮጵያ ዛሬ ተናግረዋል።

 

“በእኔ ቤተሰብ የደረሰ ልብ የሚሰብር ሀዘን በሌሎች ወገኖች ላይ ደርሶ ማየት አልፈልግም…” የሚሉት አቶ ዘውዱ ጎሳ በተለይ ልጆች በቤተሰብ ውስጥ ባሉ ችግሮችና በትምህርት ቤት አካባቢ የሚደርስባቸው የተለያዩ ተጽእኖዎች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው በትኩረት መሰራት ያለባቸው ጉዳዮች ናቸው ብለዋል።

 

ባለቤታቸውና የኤደን ወላጅ እናት ወ/ሮ በለጡ ተዘራም በየጊዜው ልጃቸውን የሚያስታውሱ ነገሮች በመፈለግ ሀዘናቸውን መርሳት እንደተሳናቸው የሚገልጹት አቶ ዘውዱ ማህበረሰባችንን በቤተሰባዊ ትምህርቶች ካልገነባን ፈተናዎችን ማብዛት ይሆንብናል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

 

ወ/ሮ በለጡ ልጃቸውን እንደንግስት ያሳደጓት መሆኑን በመግለጽ “የዚህ ሀገር ልጅ ምኑም አይታወቅም!” ሲሉ በተለያዩ መልኩ ትርጉም የሚሰጥ ቃል ተጠቅመው መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

 

ኤደን ዘውዱ በትምህርት ቤቷ ትጉ ተሳታፊ የነበረችና ኤዎችን በመደርደር የምትታወቅ ከመሆኗም በላይ በተለይ በትምህርቷ ውጭ የሆኑ ታላላቅ መጽሃፎችን በማንበብ የምትታወቅ ታዳጊ ወጣት እንደነበረች የሚያውቋት ሰዎች የመሰከሩ ሲሆን ህይወቷ ከማለፉ ከአንድ አመት በፊት ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ በትምህርት ቤታቸው ውስጥ ሊያብራራ የመጣ የመንግስት ተወካይ ለተማሪዎች ማብራሪያ ሲሰጥ ለቀረቡለት ርሃብ ነክ ጥያቄዎች ምንም አይነት ረሃብ በሀገሪቱ ውስጥ እንደሌለ በሚያስረዳበት ሰዓት የሮይትርንና የኤ.ኤፍ.ፒን ዘገባዎች እንዲሁም የቢቢሲን ትንታኔ በማጣቀስ በጥያቆዎች አጣድፋ አፍረትን አከናንባ ሸኝታው እንደነበር መምህራኖቿ ምስክርነት መስጠታቸው ተዘግቧል።

 

የዚህች ወጣት በአሳዛኝ ሁኔታ ህይወቷ ማለፍ ሀዘኑ ለመላ ቤተሰቧ ብቻ ሳይሆን ለቫንኩቨር ነዋሪዎችም ጭምር በሆኑን በመገንዘብ በቤት በወላጆች መሀከል ያሉ ችግሮችን በአደባባይ በማውጣት ለሌሎች ቤተሰቦች ትርጉም ያለው ተሞክሮዎችን ማስተላለፍ እንደሚገባ በማመን ኤደን ፕሮጄክትን በማቋቋምና ትምህርት ለመስጠት መነሳታቸውን አቶ ዘውዱ ጠቁመዋል።    

 

ፕሮጄክት ኤደን በወላጆችና በልጆች መካከል የሚከሰቱ ችግሮችንና በልጆች ላይ በቤትም ሆነ በትምህርት ቤት የሚደርስባቸውን ጥቃት (ቡሊይንግ) እንዲሁም የተለያዩ የማህበረሰባችንን ችግሮች ለማስወገድ የሚረዳ የመወያያ መድረክ ያዘጋጀ ሲሆን በተለይ በዚህ በቫንኩቨርና ሲያትል አካባቢ የሚገኙ ወገኖች ተገኝተው ልጆችን እንዴት በኖርዝ አሜሪካ ማሳደግና ከተለያዩ ችግሮች ማውጣት እንደሚቻል በርካታ ጥናቶችን በማድረግና መጽሃፍ በመጻፍ ለአማርኛ አንባቢያን ያበቃችው ደራሲ ሐምራዊት ተስፋ በምትገኝበት መድረክ ላይ እንዲገኙ ጋብዘዋል።

 

ኤደን ፕሮጄክት ያዘጋጀው ይህ መርሃ ግብር ቅዳሜ May 18,2013 ቀን ከ1 - 5pm በ 6550 Bonsor Ave. Burnaby BC የሚዘጋጅ ሲሆን በዝግጅቱ ላይ ደራሲ ሃምራዊትን ጨምሮ የተለያዩ ተናጋሪዎችና ባለፈው በደረሰባት ተደጋጋሚ ጥቃት (ቡሊይንግ) በዩ ቲዩብ ላይ በጽሁፍ በመግለጽ ራሷን ያጠፋችው ወጣት አማንዳ ቶድ ወላጅ እናት እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።(የአማንዳ ቶድን ቪድዮ ለመመልከት ይህንን ይጫኑ)   

 

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ