አባይ የህዝብ እንጂ የፖለቲካ መጠቀሚያ አይሆንም!

Ethiopia Zare (እሁድ ነኀሴ 19  ቀን 2004 ዓ.ም. August 25, 2013)የአባይ ግድብ ሂደት ግልጻማነት የጎደለውና ኢትዮጵያዊያን ያልመከሩበት አገዛዙ የፈጠረው የፖለቲካ መጠቀሚያ ነው የሚሉ ኢትዮጵያዊያን በቫንኩቨር ካናዳ የተጠራውን የግድብ ገንዘብ ማሰባሰቢያ ምሽት በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጋቸው ታወቀ።

 

 

ግድቡ የሀገሪቱ ዜጎች ያልመከሩበት፣ ለሙስና የተጋለጠና፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በአረቡ አለማት የተቀጣጠለው ህዝባዊ አመጽ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይደርስ የህዝቡን ስሜት ለመግዛት ለፕሮፓጋንዳ የተጠቀሙበት ነው ሲሉ የሚገልጹት ተቃዋሚዎች ቅዳሜ ኦገስት 24 2013 ምሽቱን በቫንኮቨር አንድ ሪስቶራንት ውስጥ እየተካሄደ ያለውን የገንዘብ ማሰባሰቢያ ምሽት ሲቃወሙ ማምሸታቸውን ለመረዳት ችለናል።

 

 

ኢትዮጵያዊያኑ በተለይ አባይ የሁላችን ሀብት ነው፣ ሁላችንም ልንመክርበት የሚገባና ልንረባረብበት የምንችልበት ታላቅ ሀገራዊ ጉዳይ ሆኖ ሳለ አገዛዙ ለፖለቲካ ትርፍ መጠቀሙ አግባብ አለመሆኑን በይፋ በመቃወም አቋማቸውን አሳውቀዋል።

 

አላማችን በህወሃት መራሹ የኢህአዴግ አገዛዝ አባላትን ብቻ ሳይሆን የወንድሞቻችንና የእህቶቻችንን ደም በማፍሰስ በመጥፎነቱ የሚታወቀው አገዛዝ የአባይ ፕሮፓጋንዳ ተጠቂ የሆኑ “የዋህ” ኢትዮጵያዊያን ለንጹሀን ደም ማፍሰሻ አገዛዙ የሚጠቀምበትን ገንዘብ ከኪሳቸው አውጥተው እንዳይተባበሩ ለማሳወቅ ነው ሲሉ አዘጋጆቹ በተለይ ለኢትዮጵያ ዛሬ ገልጸዋል።

 

“በቫንኩቨር አካባቢ የሚገኙ የህወሃት ደጋፊዎች ባስተባበሩትና ጥቂት “የዋህ” ኢትዮጵያዊያን በአባይ ልማት ፕሮፓጋንዳ የተሸወዱ ወገኖች በተሰባሰቡበት ቦታ ላይ ተቃውሟችንን የህዝብ ድምጽ እንዲሰማ ጠይቀናል ያሉ ተሰላፊዎች “አንዳንድ ወገኖች የአገዛዙና ግብረአበሮቹ መጠቀሚያ እንዳይሆኑ የሚቻለውን ትምህርት ሰጥተናል ያሉት አንድ አስተባባሪ “መንግስት አባይን በእውነት ለመገደብ ካሰበ በሀገሪቱ የፖለቲካ እርቅና ስምምነት ይፍጠር፣ በእስር የሚገኙ ንጹሀን ወገኖቻችን ይቅርታ ጠይቆ ይፍታ፣ ያኔ ለአባይ ግድብ ጥቂት አጋፋሪዎችና የተሳሳቱ ግለሰቦች ብቻ ሳይሆኑ በሙሉ ኢትዮጵያዊያን ታሪክ የምንሰራበት ሁኔታና በአጭር ተግባራዊ ምናደርግበት እውነታ ይመጣል።” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

 

 

የኢህአዴግ አገዛዝ በአባይ ግድብን ለማስገንባት በሚል በሀገር ውስጥ የመንግስት ሰራተኞችንና ነጋዴዎችን በማስገደድ ጭምር ገንዘብ እያሰባሰበ እንደነበር የተዘገበ ሲሆን በአሁኑ ሰአት ህወሃት/ኢህአዴግ በተለያዩ አለማት የሚገኙ አባላቶቹን በማስተባበር ገንዘብ ለማሰባሰብ ያወጣው እቅድ ግቡን ሊመታ እንዳልቻለ ታውቋል። 

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ