ብፁዕ አቡነ ኤልያስ Abune EliasEthiopia Zare (ሰኞ ጥቅምት 18 ቀን 2006 ዓ.ም. Oct. 28, 2013)፦ ትናንት እሁድ ኦክቶበር 27 ቀን 2013 (ጥቅምት 17፣ 2006 ዓ.ም.) በስዊድን ዋና ከተማ ስቶክሆልም የምትገኘው የመድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን ለቀድሞ የቤተክርስቲያኑ የሰበካ ጉባዔ አባላት የበጎ ሥራ የምስጋና ሽልማትና የምስክር ወረቀት ሰጠች።

 

አቶ ደሳለኝ ጭጭአይበሉ ከብፁዕ አቡነ ኤልያስ ሽልማት ሲቀበሉ

በየሣምንቱ እሁድ የሚደረገው የቅዳሴ ሥነሥርዓት ከተጠናቀቀ በኋላ በቀጠለው በዚህ የበጎ ሥራ ምስጋና ሽልማት ላይ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ በአውሮፓ፣ በምሥራቅና ደቡብ አፍሪቃ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ ተገኝተው ዝግጅቱንም በቡራኬ ከፍተዋል።

ይኽ በቤተክርስቲያን ደረጃ በአይነቱ አዲስ የሆነ የምስጋና ቀን ዋና ዓላማው ለአሥራ ስምንት ዓመታት ያህል በሰበካ ጉባዔ አባልነት ቆይተው የሥራ ጊዜያቸውን የጨረሱትን አባላት ለማመስገን ሲሆን፤ ዝግጅቱንም ያስተባበረው አዲሱ የሰበካ ጉባዔ እንደሆነ ታውቋል።

በዕለቱ የተገኙ ምዕመናን

የሰበካ ጉባዔው ሰብሳቢና የዝግጅቱ መሪ የሆኑት መላከ ፀሐይ አበበ ገላው ስለዝጅቱ አጭር ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ፤ ዶ/ር ፍቃደ ከበደ ስለዝግጅቱ እና ስለቀድሞው አባላት አሰራር ያላቸውን አስተያየት በማከል ንግግር አድርገዋል። በመቀጠልም ይኽንኑ የምስጋና ዝግጅት በተመለከተ "ሰላም ይግጠማችሁ!" የሚል ግጥም ቀርቧል።

የሰበካ ጉባዔው መዘምራን መንፈሣዊ መዝሙር ካሰሙ በኋላም፤ አቶ ታምራት አዳሙ የሰበካ ጉባዔው ምክትል ሰብሳቢ ለዘህ ዝግጅት መነሻ ስለሆነው ምክንያትና ለምን ባሁኑ ጊዜ እንደተደረገ፤ እንዲሁም አዲሱ የሰበካ ጉባዔ ከተመረጠ ጀምሮ ስለሠራው የሥራ ክንውን፣ ለወደፊቱም ያለውን ዕቅድና ዓላማ አስመልክተው ንግግር አድርገዋል።

Medhanialem  Ethiopian Orthodox church in Stockholm

በመቀጠልም አቶ እንግዳዬ "ይሄ ነበረ ክብሩ" የሚል ምክር አዘል ግጥም ካቀረቡ በኋላ የበጎ ሥራ ሽልማት ሥርዓቱ ተከናውኗል። በዚህ ሽልማት የመጀመሪያው ተጠሪ አቶ ደሳለኝ ጭጭአይበሉ የቀድሞው የሰበካ ጉባዔ ሰብሳቢ ሲሆኑ፤ ከብፁዕ አቡነ ኤልያስ እጅ ሽልማትና የምስክር ወረቀት ተቀብለዋል።

ከአቶ ደሳለኝ በኋላ በቅደም ተከተል የሰበካ ጉባዔውን ይመሩ የነበሩ ሰዎች የተዘጋጀላቸው ሽልማትና የምስክር ወረቀት የተቀበሉ ሲሆን፤ ሌሎችም ቤተክርስቲያኗን በልዩ ልዩ መልክ ያገለገሉ ሰዎች አገልግሎታችው እየተዘረዘረ የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል።

ብፁዕ አቡነ ኤልያስ ለወ/ሮ ናርዶስ ሽልማት ሲሰጡ

በመጨረሻም በብፁዕ አቡነ ኤልያስ ቡራኬ ዝግጅቱ ተጠናቆ ምዕምናኑ ምሳ ወደተዘጋጀበት አዳራሽ አምርቷል። ለመቶ ሃምሳ ሰው ከተዘጋጀው የምግብ ወጪ ውስጥ የመቶውን ሰው ወጪ የኢትዮ-ስታር ምግቤ ቤት መሸፈኑንና፤ ቤተክርስቲያኗ ለምግብ ታወጣ የነበረው ገንዘብ ተተምኖ (አስር ሺህ የስዊድን ክሮነር) ልትገነባው ላቀደችው አዲስ ሕንፃ ገቢ እንዲሆን ምግብ ቤቱ ገቢ ይደረግልኝ በማለቱ ገንዘቡ ለሕንፃ ማሠሪያው ገቢ መሆኑን መላከ ፀሐይ ለምዕመናን ገልፀዋል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ