በክዊን በርገር የተመገቡ 19 ሰዎች ታመሙ
Ethiopia Zare (ኀሙስ ሐምሌ 3 ቀን 2000 ዓ.ም. July 10, 2008)፦ ትናንት ማምሻውን ኦሎምፒያ አካባቢ በሚገኘው ”ክዊን በርገር” በተሰኘው ሐምበርገር ቤት በተበከለ ምግብ 19 ሰዎች መታመማቸውንና ወደ ሕክምና መሄዳቸውን ከአዲስ አበባ ለኢትዮጵያ ዛሬ የደረሰው መረጃ ጠቆመ።
በክዊን በርገር ሐምበርገር የተመገቡት እነዚሁ ለጊዜው ቁጥራቸው የታወቀው አስራ ዘጠኙ ሰዎች ሐምበርገሩ ውስጥ በነበረው የተበከለ/የተመረዘ ማዮኔዝ ምክንያት ክዊን በርገርን ሳይለቁ በተቀመጡበት መታመማቸውን ለማወቅ ችለናል።
እነዚሁ ሰዎች ሐምበርገሩን በልተው እንደጨረሱ ሰውነታቸው መንቀጥቀጥ፣ ከፍተኛ ትኩሳት፣ ማስመለስ እና ማስቀመጥ ያጣደፋቸው ሲሆን፣ የክዊን በርገር መጻዳጃ ቤት ተይዞባቸው የነበሩ በአካባቢው ወደሚገኙ የንግድ ተቋማት፣ ወደሚያውቋቸውና ወደየቤታቸው የሄዱ እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል።
አስራ ዘጠኙ ሰዎች በአቅራቢያው ወደሚገኘው ቤተዛታ ከፍተኛ ክሊኒክ ሄደው የሕክምና እርዳታ አግኝተው ወደየቤታቸው መሄዳቸው ታውቋል። በዚህ የምግብ መበከል/መመረዝ የተነሳ ከተጎዱት ሰዎች ውስጥ ከአንድ ቤተሰብ እናት፣ አባትና አንድ ልጃቸው እንደሚገኝበት የደረሰን መረጃ ያስረዳል።



