እነኮ/ል መንግሥቱ በእስር እንዲቀጡ የወሰኑት ዳኛ “አሸባሪዎችን በዋስ ለቀዋል” ተብለው ከሥራ ታገዱ
Ethiopia Zare (ቅዳሜ ሐምሌ 5 ቀን 2000 ዓ.ም. July 12, 2008)፦ የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ሦስት ዳኞች፣ ይሰሩበት ከነበረው የድሬደዋ ከተማ ፍርድ ቤት ጅጅጋ ከተማ ባስቻሉት ተዘዋዋሪ ችሎት በአሸባሪነት ተጠርጥረው ማረሚያ ቤት እንዲቆዩ የተደረጉ 28 ተጠርጣሪዎችን የዋስ መብት ፈቅደዋል የሚል የዲሲፕሊን ክስ ቀረበባቸው። ክሱ የደረሰው የፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ጉዳዩ እልባት እስኪያገኝ ላልተወሰነ ጊዜ የሚቆይ የእግድ ትዕዛዝ በአንዱ ዳኛ ላይ አሳልፏል።
የፍትህ ሚኒስትር መጋቢት 9 ቀን 2000 ዓ.ም. ለፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ጽ/ቤት፤ ያቀረበው የዲሲፒሊን ክስ እንደሚያስረዳው ዳኛ ኑሩ ሰዒድ፣ ከዳኛ ሀብታሙ ወርቁ እና ከዳኛ ሰዒድ ሐሰን ጋር በመሆን በሶማሌ ክልል በጅጅጋ ከተማ ባስቻሉት ተዘዋዋሪ ችሎት አሸባሪዎች ናቸው በሚል ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙ 28 ተጠርጣሪዎችን በዋስ እንዲፈቱ ትዕዛዝ ሰጥተዋል የሚል ነው።
በዳኞቹ ላይ የዲሲፕሊን እርምጃ እንዲወሰድ፣ የሚጠይቀው ይኸው የፍትህ ሚኒስቴር ክስ እንደሚያስረዳው፤ “በሶማሌ ብሔራዊ ክልል በሽብር ወንጀል የተጠረጠሩ እና ራሳቸውን ኦብነግ፣ ኦነግ እና አልኢትሃድ ብለው የሚጠሩ የ28 የአሸባሪ ድርጅት አባላት ተይዘው ለምርመራ በሶማሌ ክልል ፍ/ቤት ትዕዛዝ በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ የተደረጉ ተጠርጣሪዎችን ያሰራቸውን ክፍልና ምርመራ የሚያጣራውን ፖሊስ ሳይጠይቁት ትዕዛዝ ሰጥተዋል።” የሚል ነው።
አሸባሪ ናቸው በሚል ተጠርጥረው የታሰሩ እስረኞች፤ አብዲ ፈታህ፣ ሐሰን አብዲ፣ በሽር መሐመድ፣ አህመድ መሐመድ፣ አብዲ ሼክ፣ ሂርሲ አህመድ፣ አብዱራዛቅ ኑር፣ መሐመድ ዩሱፍ፣ መሐመድ አሊ፣ መሐመድ አህመድ፣ ዴቅ ኡስማን፣ ሙና ሲጋሊ፣ ኡመር ጣሂር፣ አብዱራህማን ሐሰን፣ ኢብራሂም ሐሰን፣ መሐመድ አህመድ፣ ሃዲ አብዲ፣ አብዱላሂ መሐመድ፣ ኡመር ሑሴን፣ አብዱራህማን ኡመር፣ ዐረብ መንታ ዓሊ፣ አብዱ መሐመድ፣ አህመድ ዩሱፍ፣ ሹክሪ ሻፊዕ፣ መሐመድ አደን፣ ሙልክ አህመድ፣ መሐመድ ሐሰን እና ሹክራ ፊሪድ ናቸው።
ክሱ አያይዞ እንደሚያስረዳው ”የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በሦስት ዳኞች አማካይነት በጅጅጋ ከተማ ከታህሳስ 14 እስከ ታህሳስ 15 ቀን 2000 ዓ.ም. ባስቻለው ተዘዋዋሪ ችሎት ተጠርጣሪዎቹ አላግባብ ታስረናል የሚል አቤቱታ በማቅረባቸው ብቻ በአጋጣሚ በሌላ ችሎት ውስጥ የነበረና ስለነዚህ ተጠርጣሪዎች ጉዳይ የማያውቅን የክልሉን ዓቃቤ ሕግ በመጠየቅ፣ ስለጉዳዩ አስተያየት እንዲሰጥበት ድንገተኛ ጥያቄ በማቅረብና ዓቃቤ ሕጉ ስለጉዳዩ የሚያውቀው ጉዳይ እንደሌለ በመግለፅ ጉዳዩን አጣርቼ መልስ ልስጥ ወይም ምርመራ የሚያጣራ ፖሊስ ይጠየቅ በማለት ቢያስረዳም ሃሣቡን ባለመቀበልና የተጠርጣሪዎቹን ምርመራውን የሚያጣራ ፖሊስ ስለተጠርጣሪዎቹ ጉዳይ ሣይጠይቁ በክልል ፍ/ቤት ትዕዛዝ ለምርመራ በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ የተደረጉትን ተጠርጣሪዎች በዋስ እንዲለቀቁ ትዕዛዝ ሠጥተዋል።” የሚል ነው።
ይኸው ክስ አያይዞ የሚጠይቀው፣ “ዳኞቹ ስለ ጉዳዩ የሚመለከተውን አካል መጠየቅ ሲገባቸው፣ ስለ ጉዳዩ ምንም እውቀት ያልነበረውን የክልሉን ዓቃቤ ሕግ በመጠየቅ ተጠርጣሪዎቹ በዋስ እንዲለቀቁ በማድረጋቸው የወ/መ/ህ/ስ/ስ/ቁ/66ትን በግልፅ የሚፃረር ድርጊት በመሆኑ ጉባዔው አቤቱታውን ከአዋጅ ቁጥር 24/88፣ ከፌዴራል ዳኞች ስነምግባር ደንብና ከፌዴራል ፍ/ቤት ዳኞች የዲሲፕሊን ክስ ስነሥርዓት ደንብ አንፃር ተመልክቶ ተገቢውን ውሣኔ እንዲሰጥበት እንጠይቃለን።” ሲል የፍትህ ሚኒስቴር ክስ ዳኞቹ በዲሲፕሊን ክስ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ጠይቋል። ከክሱ ጋር በማስረጃነት የተያያዘው ዳኞቹ ለተጠርጣሪዎቹ ዋስትና የሰጡበት ሰነድ ሲሆን፣ ሰነዱ እንደሚያስረዳው ሦስቱ ዳኞች በታህሳስ 14 እና በታህሳስ 15 ቀን 2000 ዓ.ም. ለተጠርጣሪዎቹ ጥያቄ ማቅረባቸውን ነው።
ከጥያቄና መልሱ አጠቃላይ ይዘት ለመረዳት እንደሚቻለው፣ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ለፖሊስ ቃላቸውን ከመስጠትና አንዴ ወይም ሁለቴ ፍ/ቤት ከመቅረብ ውጪ ቀጠሮ የያዘ መዝገብም ሆነ ተመላልሰው ጉዳያቸውን የሚከታተሉበት ፍ/ቤት ተወስደው እንደማያውቁ፣ ከታሰሩም ሦስት ወር፣ አራት ወር፣ ስምንት ወር፣ 10 ወር፣ 11 ወር እና እስከ አራት ዓመት ድረስ እንደሆናቸው መግለፃቸውን መዝገቡ ያስረዳል።
የተያዙትም ከደገሃቡር፣ ከዋርዴር፣ ከድሬዳዋ፣ ከጅጅጋ፣ … እንደሆነ ገልጸው፣ መምህር፣ የሻይ ቤት ሠራተኛ፣ የ10ኛ ክፍል ተማሪ፣ በሶማሌ ክልል የውሃ ቢሮ የፕላኒንግ መምሪያ ኃላፊ እንደሚገኙበት ለፍ/ቤቱ የሰጡት ቃል ያመለክታል።
ከነዚህም መካከል አቶ ሐሰን አብዲ የተባሉ ተጠርጣሪ የሰጡት ቃል ”ከታሰርኩ አራት ዓመት ሆኖኛል፤ አንድም ቀን ፍርድ ቤት ቀርቤ አላውቅም” የሚል ሲሆን፣ ተዘዋዋሪ ችሎቱ የዋስትና ጥያቄውን እንዲፈቀድለት ጠይቋል። በዚህ ተጠርጣሪ የዋስትና መብት ላይ ዓቃቤ ሕግ የሰጠው አስተያየትም ”በተጠርጣሪው ላይ የተጣራ መዝገብ አልደረሰንም፣ ፖሊስ ጣቢያ የምርመራ መዝገቡ ይኑር አይኑር የምናውቀው ነገር የለም። በመሆኑም በዋስትና ጥያቄ ላይ አስተያየት መስጠት አንችልም” የሚል እንደሆነ መዝገቡ ላይ ሰፍሯል።
ይኸው ሰነድ እንደሚያስረዳው ተጠርጣሪዎቹ ቃላቸውን በሰጡበት ወቅት አቶ አንጋው አፈወርቅ የተባሉ ዓቃቤ ሕግ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡበት ሲጠየቁ ”የምናቀርበው አስተያየት የለም፣ የተጣራ መዝገብ የለንም” ማለታቸው ዋስትና በተፈቀደበት መዝገብ ላይ ሰፍሯል።
ችሎቱም የተጠርጣሪዎቹን የዋስትና ጥያቄ ከመረመረ በኋላ ከ400 ብር ጀምሮ ዋስትና እያስያዙ እንዲለቀቁ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር። በወቅቱ የነበሩ ምንጮቻችን እንደጠቆሙት ተጠርጣሪዎቹ በዋስ ተለቀው የማረሚያ ቤቱን ግቢ ለቀው ሲወጡ በድጋሚ ተመልሰው መታሰራቸውን ነው።
በዳኞቹ ላይ የቀረበው ክስ የደረሰው የፌዴራል የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ፣ በቅርቡ ጡረታ በወጡት የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ከማል በድሪ ፊርማ በወጣ ደብዳቤ፣ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ሰጥተዋል ከተባሉት ሦስት የፌደራል ፍ/ቤት ዳኞች መካከል አቶ ኑሩ ሰዒድ ላልተወሰነ ጊዜ ከዳኝነት ሥራቸው እንዲታገዱ መወሰኑን እና ክሱ ከደረሳቸው ቀን አንስቶ በ10 ቀን ውስጥ በቀረበባቸው የዲሲፕሊን ክስ ላይ መልስ እንዲሰጡ አዘዋል።
ዳኛ ኑሩ ሰዒድ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት ጥር 3 ቀን 1999 ዓ.ም. በዋለው ችሎት በነኮሎኔል መንግሥቱ ኃ/ማርያም የክስ መዝገብ የደርግ ባለሥልጣናት በሞት እንዲቀጡ ዳኛ መድህን ኪሮስ በልዩነት ሲወስኑ፣ ተከሳሾቹ በእስራት እንዲቀጡ ብለው ከሌላ ባልደረባቸው ጋር በአብላጫ ድምፅ የወሰኑ ዳኛ ናቸው። ከእነዚህ ዳኞች መካከል አቶ መድህን ኪሮስ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሲያድጉ ሁለቱ ግን ወደ ክልል እና አነስተኛ ጉዳዮች ወደሚታዩባቸው ችሎት ተዛውረዋል።
ዳኛ ኑር ሰዒድ ከዚህ ውሳኔ በኋላ ወደ ድሬዳዋ ተመድበው የሄዱ ሲሆን፣ ከድሬዳዋ ደግሞ አሁን የተከሰሱበትን ውሳኔ በማስተላለፋቸው ተመልሰው እንዲመጡ የተደረጉ ዳኛ ናቸው።



