ፈረሰኛ ሻምበል ማሩ መልካ በ87 ዓመታቸው አረፉ!
የቀብር ስነ ስርአታቸው ዛሬ በየካ ሚካኤል ይፈጸማል
Ethiopia Zare (ረቡዕ ታህሣስ 30 ቀን 2006 ዓ.ም. Jan 8, 2014)፦ በፈረስ ግልቢያ ስፖርት ታሪክ ውስጥ በአስተማሪነት፣ በስፖርተኝነትና በርካታ ሽልማቶችን በመቀዳጀት ግምባር ቀደም ተጠቃሽ የሆኑት ፈረሰኛ ሻምበል ማሩ መልካ በ87 ዓመታቸው ታህሣስ 29 ቀን 2006 ዓ.ም ከዚህ አለም በሞት የተለዩ ሲሆን ዛሬ የቀብር ስነ ስርአታቸው በአዲስ አበባ የካ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን እንደሚፈጸም ተገለጸ።

ሻምበል ማሩ መልካ በኢትዮጵያ የፈረስ ግልቢያ ታሪክ ውስጥ ትልቅ አሻራ ያኖሩ ከመሆናቸውም በላይ በአገር አቀፍና አለማቀፍ ውድድሮች ላይ በመሳተፍ በአጠቃላይ 300 የሚደርሱ ከፍተኛ ሽልማቶችን በአሸናፊነት የተቀዳጁ ሲሆን ከ114 ጊዜ በላይ አንደኛ በመውጣት የከፍተኛ ሜዳሊያ ተሸላሚ እንደነበሩና በ42 የተለያዩ ውድድሮች ደግሞ ሁለተኛ ደረጃን በማግኘት እንደዚሁም ከ15 ጊዜ በላይ ሶስትኛ ደረጃ በመውጣት ሽልማቶችን አግኝተው እንደነበር ለመረዳት ችለናል።
ሻምበል ማሩ ህይወታቸውን በተለይ ከሚወዷቸው የውድድር ፈረሶች ጋር ያሳለፉ ሲሆን ቀድሞ ይሰሩበት ከነበረውና በርካታ ውድድሮችን በማድረግ ከሚታወቁበት ባልደራስ በጡረታ ከወጡ በኋላ በጣሊያን ኤምባሲ ፈረሰኞችን በማሰልጠንና ፈረሶችን ለውድድር በማዘጋጀት ህይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ በስራ ላይ እንደነበሩ ታውቋል።
የ9 ልጆች አባት እንደነበሩ በተለይ ለኢትዮጵያ ዛሬ የገለጹት ቤተሰቦቻቸው ሻምበል ማሩ መልካ 32 የልጅ ልጆችን እና 18 የልጅ ልጅ ልጆችን ለማየት የታደሉ የእድሜ ባለጸጋ እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል።

ህይወታቸውን ለኢትዮጵያ የፈረስ ስፖርት እድገት ሲጥሩና እስከ 87 ዓመት የህይወት ፍጻሜያቸው ጊዜ ድረስ በስራ ገበታቸው ላይ ያሳለፉት የፈረስ ስፖርት አባት ሻምበል ማሩ መልካ ህይወት ማለፍ የተሰማንን ሀዘን እየገለጽን ለመላ ቤተሰቦቻቸውና አድናቂዎቻቸው ሁሉ መጽናናትን ታገኙ ዘንድ እንመኛለን።
ኢትዮጵያ ዛሬ



