በቫንኩቨር በሳኡዲ አረቢያ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኞች 10 ሺህ ዶላር ተሰበሰበ
Ethiopia Zare (እሁድ ጥቅምት 11 ቀን 2006 ዓ.ም. Jan 18, 2014)፦ በሳኡዲ አረቢያ ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያዊያኖች ያሉበት አሳሳቢ ሁኔታ ያስጨነቃቸው በቫንኩቨር ካናዳ ነዋሪዎች ምሽቱን ባደረጉት የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ወደ 10ሺህ ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ማሰባሰባቸው ተገለጸ።
በውጭ ሀገርና በሀገር ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በሳኡዲት አረቢያ ይኖሩ ለነበሩና በሳኡድ አረቢያ መንግስት ታጣቂዎችና ጋጠወጥ የሳኡዲ ዜጎች ከፍተኛ የሆነ አሰቃቂ ግርፋት፣ ወከባ፣ አስገድዶ መድፈርና ግድያ ሲፈጸምባቸው ለቆዩ ወገኖች በተለያየ መልኩ ቁጣቸውን ሲያሰሙ የሰነበቱ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን የቫንኩቨር ነዋሪዎችም በጥቃጡ ጉዳት የደረሰባቸውን ኢትዮጵያዊያን ለመርዳት ከፍተኛ ርብርብ ሲያደርጉ እንደነበር ይታወቃል።
ይህንኑ ጥቃት ለማሰብ የብሪቲሽ ኮሉምቢያ የኢትዮጵያዊያን ማህበር በተጠራው የሻማ ማብራት ስነስርዓት ላይ የተገኙ ኢትዮጵያዊያን ባዋቀሩት ጊዜያዊ ኮሚቴ አስተባባሪነት ትላንት ጃንዋሪ 18 ቀን 2014 ዓ.ም ምሽት በተጠራ የወገን ደራሽ የእራት ጥሪ ለጊዜው ይፋ ሆኖ የታወቀ 8500 የካናዳ ዶላር የተሰበሰበ ሲሆን ጠቅላላ ገቢው ወደ 10 ሺህ ብር ይጠጋል ተብሎ ተገምቷል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ ገቢው ይፋ ሆኖ ወደተገቢው ቦታ እንደሚላክ ለማወቅ ተችሏል።
የእራት ምሽት ዝግጅቱ በፈቃደኝነት በተነሳሱ የቫንኩቨር ነዋሪ ሴት እህቶች ሙሉ ትብብር የተዘጋጀ ሲሆን እህቶች ያቀረቧቸው የባህል ልብሶችና ቁሳቁሶችም በጨረታ ተሽጠው ገቢ ማስገኘታቸው ተገልጿል።
የጊዜያዊ አስተባባሪ ኮሚቴው የህዝብ ግንኙነት የሆኑት አቶ ደበበ ጉሉ ባለፈው ሳምንት ጃንዋሪ 11 ቀን 2014 በአካባቢው ራዲዮኖች ከአይ.ኦ.ኤም ተወካይ ማሪያ ሞሬኖ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገንዘቡ ወደ አይ.ኦ.ኤም እንደሚላክ የጠቆሙ ሲሆን በቃለ ምልልሱ የቀረቡት የድርጅቱ ተወካይ የሆኑት ሚስስ ማሪያ ሞሬኖ ለአስተዳደር ወጭ የሚሆነው 10% ብቻ እንደሆነ ጠቁመው የተቀረው 90% ገንዘብ ሙሉ ለሙሉ ለጥቃቱ ሰለባዎች እንደሚደርስ አስታውቀዋል።
የእራት ምሽት ዝግጅቱ በፈቃደኝነት በተነሳሱ የቫንኩቨር ነዋሪ ሴት እህቶች ሙሉ ትብብር የተዘጋጀ ሲሆን እህቶች ያቀረቧቸው የባህል ልብሶችና ቁሳቁሶች በጨረታ ተሸጠው ገቢ ማስገኘታቸው ታውቋል።
ይህ በአይነቱ ለየት ያለና አብዛኛውን የቫንኩቨር ኢትዮጵያዊያን ያስተባበረ ዝግጅት ከአመታት በኋላ የታየና በርካቶችን ያስደሰተ ሲሆን በተለይ በዝግጅቱ የቀረቡት የሳኡዲ አረቢያ ተጠቂ ወገኖችን ስቃይ የሚያሳይ በምስል የተደገፉ ዘጋቢ ትረካዎችና ፊልሞች የበርካቶችን ልብ ሰቅሎ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።



