Ato Girma BirruEthiopia Zare (ቅዳሜ ሐምሌ 12 ቀን 2000 ዓ.ም. July 19, 2008)፦ የጅቡቲ መንግሥት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ሳይወያይና ሳይመካከር አዲስ ያወጣው ከፍተኛ የወደብ ታሪፍ ላልተወሰነ ጊዜ በሥራ ላይ እንደማይውል ታወቀ። 

 

የጅቡቲ ወደብ የታሪፍ ጭማሪ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል አሳሳቢ ሆኖ የሰነበተ ጉዳይ ሲሆን፣ የጅቡቲ መንግሥት ድንገት ስላወጣው የታሪፍ ጭማሪ ለመነጋገር የኢትዮጵያ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ ግርማ ብሩ ወደ ጅቡቲ በመሄድ ከፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጉሌህ ጋር ተነጋግረውበታል።

 

ከመጪው ኦገስት 15 ጀምሮ ተግባራዊ መሆን ይጀምራል የተባለው አዲሱ የወደብ የታሪፍ ጭማሪ መካከል የወደብ ግብር ብቻ 15 ከመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ታውቋል።

 

በማከማቻ ቦታ ላይ የተደረገው ጭማሪ ደግሞ 25 በመቶ፣ እንዲሁም በተጨማሪ ከክፍያ ነፃ ዕቃዎች የሚቀመጡበት የጊዜ ገደብ ብቻ ከ15 ቀን ወደ 7 ቀን እንዲወርድ ሊደረግ ነበር።

 

በወደቡ ላይ የተጨመረው የወደብ ኪራይ ወደቡ ውስጥ የሚገኙትን አገልግሎቶች በማግኘት የሚፈፀመውን ክፍያ እና የእፎይታ ጊዜው ማጠርም ጭምር ተዳምሮ ሀገሪቱ 22.5 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ ወጪ እንድታወጣ የሚያደርግ ነው።

 

የወደቡ የታሪፍ ጭማሪ፣ ወደብ አልባዋን ኢትዮጵያ አሁን ከምትገኝበት ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ኢኮኖሚ በተጨማሪ ወደ ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ችግር ሊያስገባ የሚችል ነው።

 

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በየዓመቱ በጅቡቲ ወደብ ለምታስገባው 4.6 ሚሊዮን ቶንስ ሸቀጣ ሸቀጥ 300 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ እየከፈለች ነው።

 

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ ከጅቡቲ ጉብኝት በኋላ የወደብ ታሪፍ ጭማሪው ላልተወሰነ ጊዜ እንዲዘገይና ሁለቱም አገሮች በጋራ በዋጋ ማስተካከያው ዙሪያ ከተስማሙ በኋላ ተፈፃሚ እንደሚሆን ተገልጿል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ