ብጹዕ አቡነ መቃሪዮስ ለሃዋርያዊ አገልግሎት ወደ ቫንኩቨር አቀኑ
Ethiopia Zare (አርብ ሰኔ 20 ቀን 2006 ዓ.ም. June 27, 2014)፦ በቫንኩቨር ካናዳ የምትገኘውን የጼዴነያ ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ቤት የሚከብርበትንና ታቦተ ህጉን ከመንበሩ ለማስገባት ወደ አካባቢው ሀዋርያዊ ጉዞ የሚያደርጉት ብጹእ አቡነ መቃርዮስ ነገ በስፍራው የወንጌል ትምህርት እንደሚሰጡ ተገለጸ።
በአውሮፓ የተለያዩ ሀገራት በመዘዋወር ተመሳሳይ ሃዋርያዊ ጉዞ አድርገው በተለይ በውስጥ አለመግባባት የሚከሰቱ የቤተ ክርስቲያን ችግሮች ዙሪያ ምእመናንንና ካህናትን በጾምና በጸሎት በመታገዝ በርካታ ችግሮችን እንደፈቱ የሚታወቁት አቡነ መቃርዮስ ሃዋርያዊ አገልግሎታቸውን በመቀጠል ወደ ቫንኩቨር ካናዳ አምርተዋል።
በቫንኩቨር ካናዳ የጼዴነያ ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ላለፉት አራት አመታት አሁን በአጸደ ስጋ የሌሉት ብጹእ አቡነ ዜና ማርቆስ ባርከው በላኳቸው መላከ ጸሀይ አፈወርቅ በመታገዝ ምእመናን ሃይማኖታቸውንና ሀገራቸውን ጠንቅቀው እንዲያውቁ በማስተማርና በመምከር አገልግሎት በመስጠት ላይ የምትገኝ መሆኗንና ቤተ ክርስቲያኗ ለ120 አመት ያገለገለና በከተማው በቅርስነት የተመዘገበ ቋሚ ቤተ መቅደስ ማግኘቷን የገለጹት የሰበካ ጉባኤ አባላት አሁንም በእመቤታችን ቀን ነገ ቅዳሜ ሰኔ 21/2006 ዓ.ም (ጁን 28 ቀን 2014 ዓ.ም) ቅዳሴ ቤቱ የሚከብርበትና ታቦተ ህጉ በሚገባበት እለት ቅዱስ አባታችን አቡነ መቃርዮስን ለሃዋርያዊ አገልግሎት መጋበዛቸውን የገለጹ ሲሆን መላ ምእመናን በ628 Royal Ave. በሚገኘው ቤተ ክርስቲያን ከጠዋቱ 6AM ጀምሮ በመገኘት የበረከቱ ተካፋይ እንዲሆኑ በቫንኩቨርና አካባቢው የሚገኙ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታይ ወገኖችን ጨምሮ በሲያትል፣ በፖርትላንድ፣ በካልጋሪና አካባቢው የሚገኙ ምእመናን ተጋባዥ መሆናቸውን የሰበካ ጉባኤው አክለው ገልጸዋል።



