የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በየመን እገታ መፍትሄ አላገኘም
ወደ ኢትዮጵያ እንዳይተላለፉ ስጋቱ አይሏል
“ኤርትራዊያኖች የየመን አየር መንገድን እንዳይጠቀሙ ማስተባበር ያስፈልጋል” አቶ ዳንኤል ጥላሁን (የህግ ባለሙያ)
Ethiopia Zare (ሐሙስ ሰኔ 26 ቀን 2006 ዓ.ም. July 3, 2014)፦ የግንቦት ሰባት ንቅናቄ ዋና ጸሃፊ የሆኑት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ለጉዞ መሸጋገሪያ የመን ከገቡ ጀምሮ በአገሪቱ ደህንነቶች ታፍነው መወሰዳቸውን አስመልክቶ ኢትዮጵያዊያን ቁጣቸውን እያሰሙ ሲሆን በተለይ የየመን አየር መንገድን በመቃወም ኤርትራዊያን የጉዞ ማእቀብ እንዲያደርጉ አንድ ተቀማጭነቱን ካናዳ ያደረገ የህግ ባለሙያ ጥሪ አቀረበ።
በህግ የማስትሬት ዲግሪውን በእንግሊዝ ሀገር የሰራው አቶ ዳንኤል ጥላሁን ለኢትዮጵያ ዛሬ እንደገለጸው አቶ አንዳርጋቸው ያሉበት ሁኔታ እጅግ የሚያሳዝን ቢሆንም በአለማቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያዊያኖች ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ በተጨማሪ ኢትዮጵያዊያኖችን ጨምሮ በተለይ የኤርትራና የሱማሌ ዜጎችም በየመን አየር መንገድ የሚያደርጉትን ጉዞ ከፍተኛ የየመን የገቢ ምንጭ እንደመሆኑ ጉዟቸውን በመሰረዝ ትብብር እንዲያደርጉ መሰራት እንዳለበት ጠቁሟል።
የአቶ አንዳርጋቸውን እገታ አስመልክቶ በርካታ አለማቀፍ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ሲሆን የፖለቲካ ድርጅቶችም ተቃውሟቸውን በማሰማት ላይ ይገኛሉ። ዛሬ ሳንሆዜ በመካሄድ ላይ ባለው የሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያዊያኖች የእግር ኳስ የስፖርት ውድድር ዝግጅት ላይ የኢትዮጵያ ሳተላይት ድርጅት ባሰናዳው ስብሰባ ላይ ተጋባዥ የሆኑት የግንቦት ሰባት ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ አቶ አንዳርጋቸው ተላልፈው ስለመሰጠታቸው የሚጠቁም ንግግር ያደረጉ ሲሆን በእርግጥ ለህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ ተላልፈው ስለመሰጠታቸው ለማረጋገጥ ያደረግነው ጥረት እስካሁን አልተሳካም።
የአቶ አንዳርጋቸው መታገትም ሆነ ተላልፎ መሰጠት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ያለውን እንድምታ አስመልክቶ ጥያቄ የቀረበለት አቶ ዳንኤል ጥላሁን “የመን አቶ አንዳርጋቸውን ለሶስተኛ ሀገር አሳልፎ የመስጥ ህጋዊነት የላትም፤ የሚጠበቅባት አቶ አንዳርጋቸው መሸጋገሪያ ፈቃድ አለመስጠት ብቻ ሆኖ ሳለ አንድን የሌላ አገር ዜጋ ለሶስተኛ ሀገር አሳልፋ የምትሰጥበት ህጋዊ አሰራር የለም ብሏል። በማያያዝም አቶ አንዳርጋቸው በአለማቀፍ ደረጃ በሽብርተኛነትም ሆነ በሌላ ወንጀል የማይፈለግ በመሆኑ የአንዲት ሀገርን (ኢትዮጵያ) ፍርድ ምክንያት አድርጎ አሳልፎ መስጠት በኢትዮጵያና በየመን መካከል ታሪካዊ ቅሬታን መጫር ብቻ ሳይሆን የእንግሊዝ መንግስትም ለዜጎቹ ያለውን አቋምና ጥንካሬ የሚፈታተን ነው።” በማለት አስረድቷል።
የአቶ አንዳርጋቸው ሁኔታ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ያለውን እንድምታ አስመልክቶም በሁለትዮሽ እንደሚያየው የገለጸው አቶ ዳንኤል “ለጊዜው መደናገጥንና ተስፋ አስቆራጭ የሚመስሉ እውነታዎች ቢኖሩም ‘እኔን አይነኩኝም’ በማለት የተዘናጋውን ኢትዮጵያዊ ደህንነት ስጋት ውስጥ ስለሚከት የተቃዋሚውን ጎራ ሊያጠናክረው ይችላል።” ሲል አስተያየቱን አክሎ ገልጿል።
አቶ ዳንኤል በተጨማሪም በየመን የሚገኙ በርካታ የኢትዮጵያን ሁናቴ የተገነዘቡና በሀገሪቱ ተጽእኖ ማሳደር የሚችሉ ሰዎች ጋር ግንኑነትን በአስቸኳይ ማጠናከር ግንቦት ሰባትም ሆነ ሌሎች ድርጅቶች ፈጣን እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ አስገንዝቧል።



