አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ተላልፈው ተሰጡ
“የተፈጠረው ሁናቴ እጅግ ቢያሳዝንም ይህንን አለማቀፍ ህግ የሚጥስ አገዛዝ ለመጣል ሁላችንም ቆርጠን እንድንነሳ ያደርጋል” አቶ ነአምን ዘለቀ
Ethiopia Zare (ሐሙስ ሰኔ 26 ቀን 2006 ዓ.ም. July 3, 2014)፦ ከዱባይ ወደ አስመራ በመጓዝ ላይ የነበሩትና የመን ውስጥ ሰንዓ ከተማ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለትራንዚት የወረዱት የግንቦት ሰባት ንቅናቄ ዋና ጸሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እዛው የመን ታግተው ከቆዩ በኋላ ለኢትዮጵያ መንግሥት ተላልፈው መሰጠታቸው ተረጋገጠ።
አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በየመን የጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር የዋሉት ሰኔ 16 ቀን 2006 ዓ.ም ሲሆን ድርጅታቸው ግንቦት ሰባት ከእስር የሚፈቱበትን መንገድ ለማመቻቸት የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቶ እንዳልተሳካለት በመግለጽ ከሦስት ቀናት በፊት ሁኔታውን ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።
ዛሬ ሰኔ 26 ቀን 2006 ዓ.ም የአቶ አንዳርጋቸው ተላልፎ መሰጠት በተለያየ መልኩ ሲነገር ቆይቶ በካሊፎርኒያ ግዛት በሳንሆዜ ከተማ እየተከበረ በሚገኘው የኢሳት አራተኛ ዓመት በዓል ላይ ተግኝተው ንግግር ያደረጉት የግንቦት ሰባት ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፤ ሰኔ 16 ቀን በየመን ሰንዓ በጸጥታ ኃይሎች ተይዘው የነበሩት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ለኢትዮጵያ መንግሥት ተላልፈው መሰጠታቸውን አረጋግጠዋል።
ተላልፈው መሰጠታቸውን ዛሬ ጠዋት ማረጋገጣቸውን በተለይ ለኢትዮጳያ ዛሬ የገለጹት አቶ ነአምን ዘለቀ “ሁኔታው እጅግ ቢያሳዝንም የአለማቀፍ ህግን እየጣሱ የሁሉንም ሰው አንገት የሚያንቁ ከሆነ ሁላችንም እስከምን ቆርጠን በመነሳት ይህንን አገዛዝ እስከመጨረሻው የምንተናነቅበት የትግል ደረጃ ላይ እንደደረስን ያስረዳል።” በማለት ቁጭታቸውን ገልጸዋል።
በንግግራቸውም፤‹‹እንዲህ አይነት ውሳኔ ውጤት አለው። ያን ውጤት ደግሞ ያዩታል። ከዚህ በኋላ እንደ በፊቱ ተጎጂ ሆነን ስንመታ እያለቀስን የምንኖበት ጊዜ አብቅቷል። ካሁን በኋላ ብንወድቅ እየታገልን፣ ብንሞት እየገደልን ነው የምንሞተው።›› በማለት ገልጸዋል። አቶ አንዳርጋቸው የመን ውስጥ ሲያዙ መጀመሪያ ላይ የተሰጣቸው ምክንያት የመግቢያ ቪዛ አልያዙም የሚል ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ተላልፈው መሰጠታቸው ግን ቀድሞውኑ የኢትዮጵያ መንግሥት እጁ እንዳለበት ማረጋገጫ ሆኗል።
አቶ አንዳርጋቸው በዚህ አየር መንገድ ሲተላለፉ ይህ የመጀመሪያቸው ባለመሆኑ እንቅስቃሴያቸውን ሲከታተል የቆየ አካል ሆን ብሎ በቁጥጥር ስር ሳያደርጋቸው እንዳልቀረ ተገምቷል። አቶ አንዳርጋቸው የእንግሊዝ ዜግነት ያላቸው በመሆኑ በየመን የሚገኘው የእንግሊዝ ኤምባሲ መረጃው ሲደርሰው ዜጋውን ለማግኘት ያደረገው ጥረት ያልተሳካለት ሲሆን አቶ አንዳርጋቸው የመን ውስጥ ናቸው በተባለበት ወቅት እርሳቸው ወደ ኢትዮጵያ ተላልፈው ሳይሰጡ እንዳልቀሩ ተገምቷል። አቶ አንዳርጋቸው በ1997 ዓ.ም ቅንጅትን ተቀላቅለው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል በመሆን በተለይ በሰነድ ዝግጅት ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ ሲያደርጉ እንደነበር በወቅቱ አብረዋቸው የሰሩ ሰዎች ምስክርነታቸውን ይሰጡላቸዋል። በዛን ወቅትም ዝዋይ እስር ቤት ገብተው ከፍተኛ ድብደባ የደረሰባቸው ሲሆን በውጭ አገርና በአዲስ አበባ የሚገኙ ቤተሰቦቻቸው በጋራ በመሆን ባደረጉት ጥረት ከእስር ተለቀዋል። ‹‹ነጻነትን የማያውቅ ነጻ አውጪ›› ጸሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ከተሰደዱም በኋላ የኢትዮጵያን ጉዳይ በሚመለከት በርካታ ጥናቶችን በማድረግ የተለያዩ ጹሑፎችን ሲያወጡ ቆይተው ኢትዮጵያን ከአምባገነን ስርአት ለማውጣት ባመኑበት መንገድ እስከ ለመታገል ያስችለናል ያሉትን ግንቦት ሰባት ከአጋሮቻቸው ጋር ማቋቋማቸው ይታወቃል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ የድርጅቱ አመራር አባል የሆኑት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞና አቶ አሳምነው ጽጌ ጋር አገር ውስጥ በህቡዕ ተደራጅተው መንግሥትንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማፍረስ ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል በሚል ክስ ተመስርቶባቸው እንደነበር ይታወሳል። ፍርድ ቤቱም እነ ጄኔራል ተፈራ ማሞ በዕድሜ ልክ እስራት እንዲቀጡ ሲወስን፣ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋና አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በሞት እንዲቀጡ መወሰኑ ይታወሳል።



