የጁላይ ሃያው የሲያትሉ ህዝባዊ ውይይት (ሪፖርታዥ)
”እንደትናንቱ ሁሉ ዛሬም አብራችሁን እንድትሆኑ እጠይቃለሁ” አቶ አስራት ጣሴ
”ለአኝዋክ ህዝብ ብቻ መታገል መፍትሔ አያመጣም” አቶ ኦባንግ ሜቶ
”በዓለም ላይ ካሉ ሀገሮች ምንም ሥራ የማይሠራው የአቶ መለስ ዜናዊ መንግሥት ብቻ ነው” ፕ/ር አለማየሁ ገ/ማርያም
”ኢትዮጵያዊነታችሁ የማትገላገሉት ስለሆነ የምትኮሩባት ኢትዮጵያ እንድትሆን መታገል አለባችሁ” ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም

Ethiopia Zare (ሰኞ ሐምሌ 14 ቀን 2000 ዓ.ም. July 21, 2008)፦ ትናንት እሁድ ሐምሌ 13 ቀን 2000 ዓ.ም. አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ በሲያትል ከህዝብ ጋር ያደረገው ውይይት በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁ ታወቀ። በዚህ ህዝባዊ ውይይት ላይ ተጋባዥ ተናጋሪዎች የነበሩት ፕ/ር መስፍን ወልደማርያምና አቶ አስራት ጣሴ ከአንድነት ፓርቲ፣ ፕ/ር አለማየሁ ገ/ማርያም እና አቶ ኦባንግ ሞቶ ናቸው።

የህዝባዊ ውይይቱ አጀንዳ ኢህአዴግ በቅርቡ ለሱዳን አሳልፎ ሰጥቷል ስለሚባለው የኢትዮጵያ ምዕራባዊ ድንበር እና በወቅታዊ የሀገር ጉዳዮች ላይ የነበረ ሲሆን፣ በውይይቱ ላይ ወደ 200 የሚጠጉ ሰዎች ተካፍለዋል። ውይይቱ ከሰዓት በኋላ 1 ፒ.ኤም. ይጀመራል ተብሎ የነበረ ቢሆንም፣ አንድ ሰዓት ዘግይቶ ነበር የተጀመረው።ይጠናቀቃል ተብሎ የታቀደው ደግሞ 5 ፒ.ኤም. ቢሆንም 6፡30 ፒ.ኤም. ላይ ተጠናቅቋል። ህዝባዊ ውይይቱን ያዘጋጀው በሲያትል የአንድነት ፓርቲ ድጋፍ ማኅበር ነበር።
የመጀመሪያው ተናጋሪ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ የላዕላይ ምክር ቤት አባልና የፓርቲው ዋና ፀሐፊ የሆኑት አቶ አስራት ጣሴ ሲሆኑ፣ ንግግራቸውን የጀመሩት በውጭ ሀገር ላሉ ኢትዮጵያውያን ምስጋና በማቅረብ ነበር። አክለውም ”እንደትናንቱ ሁሉ ዛሬም አብራችሁን እንድትሆኑ እጠይቃለሁ” በማለት ተናግረዋል።
አንድነትን በሚመለከት በሰጡት አስተያየት ላይ ”ቅንጅትን ወደ አንድነት የቀየርንበት ምክንያት ተገድደን እንጂ ወድደን አይደለም። በእርግጥ ቅንጅት የኢትዮጵያ ህዝብ የደገፈው፣ የመረጠው፣ በህዝቡ ልብ ውስጥ የገባ ቢሆንም፤ ለኢትዮጵያ ያለን ራዕይ ከስም አምልኮት በላይ በመሆኑ አንድነት ፓርቲ የቅንጅት ሞራላዊ ወራሽ ነው። የትግል ስልቱ በሠላማዊ መንገድ መሆኑ አማራጭ የሌለው ነው።” በማለት አቶ አስራት ተናግረዋል።
በሁለተኛ ተናጋሪነት የቀረበው አቶ ኦባንግ ሜቶ ሲሆን፣ ”እኔ እንኳን ወደ ፖለቲካው ሳይሆን፣ የሰብዓዊ መብት ታጋይ ነኝ ብል ይሻላል። የሰብዓዊ መብት ጥያቄን የማቀርበው ለጋምቤላ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያ ነው። ...” ብሏል።
አቶ ኦባንግ ይህንንም ሲያብራራ ”ዲሲ ኮንግረስ ላይ ንግግር ለማድረግ ሄጄ ነበር። ባጋጣሚ የተቀበለኝ ባለታክሲ ግርማ ነጋሽ የሚባል ኢትዮጵያዊ ነበር። ‘ከየት ነህ?’ ብሎ በእንግሊዝኛ ጠየቀኝ። ‘ከየት እመስልሃለሁ፣ ገምት’ አልኩት - በእንግሊዝኛ። ሁሉንም የአፍሪካ ሀገሮችን ጠርቶ ሦስት ሀገሮች ግን ሊጠራ አልቻለም። ሦስቱ ሀገሮች ኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሶማሌ ነበሩ። ሲደክመው ’ንገረኝ ወይንም ምርጫ ስጠኝ’ አለኝ። ‘ኤ - ኢትዮጵያ፣ ቢ - ኤርትራ፣ ሲ - ሶማሊያ፣ ዲ - ከተጠቀሱት ውጭ’ አልኩት። የመለሰልኝ መልስ ’ዲ - ከተጠቀሱት ውጭ’ የሚለውን ነበር። ለአኝዋክ ህዝብ ብቻ መታገል መፍትሔ እንደማያመጣ ተገነዘብኩ። እናም ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ለአማራው፣ ለትግሬው፣ … መታገል እንዳለብኝ ወሰንኩ ...
”... ለመላው ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ካልተከበረ ለአኝዋክ ህዝብ ሊከበር አለመቻሉን ከታክሲ ሹፌሩ ግርማ ነጋሽ ተረዳሁ። ” ካለ በኋላ ወያኔ/ኢህአዴግን በሚመለከት ”... ወያኔ ትግሬ ብቻ አይደለም፣ አማራ ወያኔ አለ፣ ትግሬ ወያኔ አለ፣ ኦሮሞ ወያኔ አለ፣ አኝዋክ ወያኔ አለ፣ ... እነሱ ባይኖሩ፤ ወያኔ አትኖርም ነበር። እኔ ግን በአንድ ነገር አምናለሁ። ምዕራባውያንና ቻይኖች ... ኢትዮጵያን ሊረሱ ይችላሉ። እግዚአብሔር ግን ኢትዮጵያን አይረሳም።” በማለት ተናግሯል። አቶ ኦባንግ ባደረገው ንግግር የአድማጮችን ልብ ስቦና አስደምሞ ነበር።
ሦስተኛ ተናገሪ የሰብዓዊ መብት ተሟጋችና ኤች.አር. 2003 ብዙ ደረጃዎችን እንዲያልፍና አሁን ያለበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በግንባር ቀደም በመሆን እየታገለ ያለው ፕ/ር አለማየሁ ገ/ማርያም (አልማሪያም) ነበር።
ፕ/ር አለማየሁ የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ኮሚቴ አባል እንደመሆኑ መጠን፣ ንግግሩን በአብዛኛው በድንበር ጉዳዩ ላይ ያደረገ ሲሆን፤ ”ዜናዊ (መለስ ዜናዊ) በድንበሩ ጉዳይ ላይ ለእኛ ለኢትዮጵያኖች ’የራሳቸውን መሬት ሰጥቻቸዋለሁ’ እንደሚለን ሁሉ፤ ለሱዳኑ መሪ ለአልበሽር ተቃራኒ ነገር ሊናገር እንደሚችል መገመት አያዳግትም። እኛ አሁን በድንበሩ ጉዳይ ላይ ተወጥረናል ማለት፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ረሃብ፣ ወይንም የዴሞክራሲያዊና የሰብዓዊ መብት ዕጦትን ረሳን ማለት አይደለም። ሁሉንም እንደአመጣጣቸው መታገል አለብን” ሲል ከመናገሩም በላይ ”እኛ በዲሞክራሲ፣ በሰብዓዊ መብት መከበር፣ የሕግ የበላይነት በሀገሪቱ ውስጥ መስፈን ላይ እስከተስማማን ድረስ፤ በተስማማንበት ጉዳይ ላይ በጋራ መሥራት ይኖርብናል” ሲል በአጽንኦት ተናግሯል።
”ከዓለም ካሉ ሀገራቶች ምንም አይነት ሥራ ከማይሠሩ መንግሥታት ውስጥ አንዱ የዜናዊ መንግሥት ነው። ይህንን ስታትስቲክስ ለማውጣት ባለሙያዎች የሚጠቀሙት በሀገር ውስጥ የነዋሪዎች ከቦታ ቦታ መፈናቀል፣ የተማሩና የተሻለ ኑሮ ያላቸው ወደውጭ መውጣትን ጨምሮ 80 በመቶው የሚሆነው የሀገሪቱ ህዝብ በአማካይ የቀን ገቢው ከ2 ብር በታች ከመሆኑም በላይ አንድ በመቶ የሚሆነው ባለሀብት ከደሃው ማኅበረሰብ በእጅጉ ተራርቆ ይኖራል” ሲል ምሁራዊ ጥናቱን አብራርቷል።
ፕ/ር አለማየሁ በቅርቡ ”Failed leader + failed regime = failed state, Why is "Ethiopia a failed state?" በሚል ርዕስ በተለያዩ ድረ ገጾች ላይ ያቀረበውን ጽሐፍ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!
የመጨረሻው ተናጋሪ የነበሩት የኢሰመጉ መስራችና የአንድነት የላዕላይ ም/ቤት አባል የሆኑት ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም ”በእስር በነበርንበት ጊዜ ፀሐይ፣ በረዶ፣ ውርጭ፣ ... ሳትሉ እኛን ለማስፈታት ስትጮሁልን እንደነበር በተለያዩ ራዲዮኖች ሰምቻለሁ። ለዚያም ትልቅ ምስጋና ይገባችኋል። አንዳንዴ ሳስበው የእናንተን አንድነት ለማየትና የኢትዮጵያን ህዝብ አንድ ለማድረግ ደግመን ቃሊቲ እንግባ ይሆን? እላለሁ። ...” በማለት በምስጋና ነበር ንግግራቸውን የጀመሩት።
በመቀጠልም ”... መልዕክቴን በጽሑፍ ለማቅረብ ተዘጋጅቼ ነበር። የኦባንግን ንግግር ከሰማሁ በኋላ በቃሌ መናገርን መረጥሁ። ኦባንግ ሁሉንም ነገር አስቀምጦታል። ...” ብለዋል።
ፕ/ር መስፍን ”እኔ አሁን በኢትዮጵያ ያለውን መንግሥት አልለውም። አገዛዝ ነው የምለው። በህዝብ የተመረጠ፣ ለህዝብ የሚታዘዝ መንግሥት በኢትዮጵያ ቢመጣ በአጭር ጊዜ የአፍሪካ ጃፓን መሆን እንችላለን።” በማለት ሲናገሩ ተሰብሳቢው በጭብጨባ አጅቧቸዋል።
”የሚያስተባብረን፣ የሚመራን፣ የምንቆጣጠረው፣ የምናዘው፣ ... መንግሥት ነው ያጣነው።” ካሉ በኋላ ”ኢትዮጵያዊነታችሁን የትም ብትሄዱ አይለቃችሁም። እዚህ አሜሪካም ብትመጡ ኢትዮጵያዊ ናችሁ። አሜሪካዊ ዜግነት ብትቀበሉም ኢትዮጵያዊ አሜሪካዊ ናችሁ። ኢትዮጵያዊነታችሁን የምትገላገሉት ጉዳይ አይደለም። የማትገላገሉት ከሆነ ደግሞ የምትኮሩባት ኢትዮጵያ እንድትሆን መታገል አለባችሁ።” በማለት የተናገሩ ሲሆን፣ በተጨማሪም ”በዓለም ደረጃ በተከሰተው የምግብ ችግር ምክንያት በአፍሪካ፣ በእስያና በሌሎች ሀገራት በምግብ ዋጋ መናር ምክንያት ሠላማዊ ሰልፍ ይወጣል። በጣም የሚያሳዝነው በኢትዮጵያ ግን አይወጣም። ህዝቡ ሰልፍ የሚያደርገው በየቤተክርስቲያኑ ነው።” ሲሉ ተደምጠዋል።
ፕሮፌሰሩ በተለይ ሠላማዊ ትግልን በሚመለከት በአጽንኦ የተናገሩ ሲሆን፣ በተለይ የወያኔ/ኢህአዴግን ጭካኔ በሚመለከት አጸፋ የሚሆን የትጥቅ ትግል ያስፈልጋል የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ቀርቦላቸው ነበር። ፕሮፌሰሩ ”አገዛዙ ጨካኝና አረመኔ መሆኑ ምንም ጥያቄ የሌለው ጉዳይ ነው” በማለት በኢሰመጉ በነበሩበት ወቅት ያዩትን ዘግናኝ ሁኔታ አውስተዋል።
”አንዷ እናት ልጅሽ ሸፍቷል በማለት ወስደው አስረው፣ አሰቃይተው፣ ጫካ ወስደው ከሌላ ልጇ ጋር ገደሏት። አልቀበሯትም። ሌላዋ ሴት እንደዚሁ ’የሸፈተ ልጅሽ የት እንዳለ ታውቂያለሽ’ በማለት ማጥበቂያ ባለው ሽቦ እጇን አስረው ሽቦው እጆችዋን ሰርስሮ ሽባ እስኪያደርጋት ካሰቃዩዋት በኋላ እኛ ቢሮ መጥታ በዓይኔ አይቻለሁ። እንደዚህ አይነቱን ጭካኔ በሚመለከት ከእኔ በላይ ያያችሁ አይመስለኝም። እኛም ጭካኔ የምንጀምር ከሆነ ተያይዘን ገደል ነው የምንገባው። ይሄንን ማስቆም የምንችለው በፍቅር ነው። ...” ሲሉ አባታዊ ምክራቸውን ሰጥተዋል።
አራቱ ተናጋሪዎች ንግግራቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ከተሰብሳቢዎች ለመድረኩ ለተሰነዘሩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተናጋሪዎቹ ምላሽ ሰጥተዋል።



