ደራሲ መስፍን ሀብተማርያም Mesfin HabtemariamEthiopia Zare (ማክሰኞ ሐምሌ 8 ቀን 2006 ዓ.ም. July 15, 2014)፦ ከአቶ ሀብተማርያም ሞገስ እና ከወ/ሮ ደስታ አየለ በ1935 ዓ.ም. የተወለዱት ደራሲ መስፍን ሀብተማርያም እሁድ ሐምሌ 6 ቀን 2006 ዓ.ም. በ71 ዓመታቸው በአዲስ አበባ ከተማ አረፉ።

ደራሲ መስፍን በልጅነታቸው ባህላዊ የቤተ ክህነት ትምህርት የተማሩ ሲሆን፣ በሞጆና በአንቦ የአንደኛና የሁለተኛ ደራጃ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል። በወቅቱ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተብሎ በሚጠራው የትምህርት ተቋምም በመግባት በቋንቋዎችና ሥነ-ጽሁፍ በማዕረግ ተመርቀው የቢኤ ዲግሪ አግኝተዋል። በመቀጠልም ካናዳ በሚገኘው ቫንኩቨር ከተማ በመሄድ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ብሪቲሽ ኮሎምቢያ ገብተው በፈጠራ ሥነ- ጽሁፍ የማስተርስ ዲግሪ አግኝተዋል።

ደራሲ መስፍን ሀብተማርያም አገራቸው ከተመለሱ በኋላ በአማርኛ ቋንቋ በኢልብወለድ አጻጻፍ የትምህርት መስክ በተለያዩ ቦታዎች አስተምረዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም በቋንቋዎች ጥናት ተቋም የስነጽሁፍ ኮርሶችን በመስጠት ቆይተዋል። ከዚህም በተጨማሪ በኢትዮጵያ ራዲዮና በኩራዝ አሳታሚ ድርጅትም ሠርተዋል።

በህዝብ ዘንድ ከሚታወቁባቸው ድርሰቶቻቸው መካከል “የቡና ቤት ስዕሎችና ሌሎች ወጎች”፣ “አዜብና ሌሎች አጫጭር ልብወለዶች”፣ “ዓውደ አመት እና የለሊት ድምጾችና ሌሎች ወጎች” ቅድሚያውን ስፍራ የያዙ ሲሆኑ፣ በራዲዮና በቴሌቭዥን የሚነበቡ ምርጥ ሥራዎች ነበሯቸው።

ደራሲ መስፍን የሚጽፏቸው ጽሁፎች ከትምህርት ሰጪነታቸው እኩል የማዝናናትም ኃይል እንዳላቸው የሚመሰክሩት አንባብያን ብቻ ሳይሆኑ ደራሲያኑም ጭምር ናቸው። በተለይም ባለቅኔ ደራሲና መምህር ደበበ ሰይፉ ይበልጥ አድናቂያቸው እንደነበሩ ይነገራል። እንዲሁም የሳቸውን ሥራ በመመርኮዝ የመመረቂያ ጽሁፍ ያቀረቡም ብዙዎች ናቸው።

ደራሲው በራሳቸው ፈቃድ ሥራቸውን ለቀው ከሥነ-ጽሁፍ ሙያ ጋር የተያያዙ ልዩ ልዩ ሥራዎችን በመሥራት የቆዩ ሲሆን፣ ሐምሌ 6 ቀን 2006 ዓ.ም.፣ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ጋዜጠኛ ደራሲና አርታኢ መስፍን ሀብተማርያም ባለትዳርና የአምስት ልጆች አባት ነበሩ።

የኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል ለደራሲ መስፍን ሀብተማርያም ቤተሰቦች፣ ወዳጅና ዘመዶች፣ እንዲሁም ለመላው አፍቃሪዎቻቸው መጽናናትን ይመኛል። 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ