የዐቃቤ ሕግ የመሰረተውን ሙሉ ክስ ይዘናል
የዋስትና መብት ተከልክለው ወደቃሊቲና ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ተወሰዱ፣ ለሐምሌ 28 ተቀጠሩ
የታሰሩት ስድስት ጦማርያንና ሦስት ጋዜጠኞች The jailed 6 bloggers and 3 journalists

Ethiopia Zare (ዓርብ ሐምሌ 11 ቀን 2006 ዓ.ም. July 17, 2014)፡- ዛሬ ጠዋት በ84 ቀናቸው በልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተሰየመ ችሎት ስድስቱ ጦማርያን በፍቃዱ ኃይሉ፣ ናትናኤል ፈለቀ፣ ማህሌት ፋንታሁን፣ አጥናፉ ብርሃኔ፣ ዘለዓለም ክብረት፣ አቤል ዋበላ እና ሦስቱ ጋዜጠኞች አስማማው ኃይለ ጊዮርጊስ፣ ኤዶም ካሣዬና ተስፋለም ወልደየስ ዐቃቤ ሕግ የመሰረተባቸው የክስ ፋይል ለመጀመሪያ ጊዜ ደርሷቸዋል።

ዐቃቤ ሕግ ፖሊስ በቁጥጥር ስር ካዋላቸው ስድስቱ ጦማርያንና ሦስት ጋዜጠኞች በተጨማሪ፤ ጦማሪ ሶልያና ሽመልስ በሌለችበት ክስ መስርቶባታል። ዐቃቤ ሕግ በአስሩም ላይ ሁለት አይነት ክስ የመሰረተ ሲሆን፣ 1ኛው ክሱ "በ1996 ዓ.ም. የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1)፣ ሀ እና ለ 38 (1) እና (2)፣ በፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 4 ላይ የተመለከተውን መተላለፍ" የሚል ነው። 2ኛው ክሱ ደግሞ "በ1996 ዓ.ም. የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 27/1/ሀ/ለ፣ 32(1)/ሀ እና ለ፣ 38(1) እና አንቀጽ 238/1/ሀ ስር ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ" የሚል ነው። ሙሉውን የዐቃቤ ሕግ የክስ ዝርዝር በፒ.ዲ.ኤፍ. ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!

የተከሳሾች ጠበቆች የደንበኞቻቸው የዋስትና መብት እንዲከበር ለፍርድ ቤቱ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት ያላገኘ በመሆኑ ጋዜጠኛ ኤዶም ካሣዬ እና ጦማሪት ማኅሌት ፋንታሁን ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ሲወሰዱ፤ ቀሪዎቹ ጦማርያን በፍቃዱ ኃይሉ፣ ናትናኤል ፈለቀ፣ አጥናፉ ብርሃኔ፣ ዘለዓለም ክብረት፣ አቤል ዋበላ እና ሁለቱ ጋዜጠኞች አስማማው ኃይለ ጊዮርጊስ እና ተስፋለም ወልደየስ ወደ ቂሊንጦ እስር ቤት ተወስደዋል። በሌለችበት ክስ የተመሰረተባት ጦማሪት ሲሊያ ሽመልስ ደግሞ በጋዜጣ ጥሪ እንዲቀርብላት ተወስኗል። የዕለቱ ችሎት ለሰኞ ሐምሌ 28 ቀን ቀነ ቀጠሮ በመስጠት ተበትኗል።

ስድስቱ ጦማርያንና ሦስቱ ጋዜጠኞች ላለፉት 84 ቀናት በማዕከላዊ ምርመራ ከሰው ጋር እንዳይገናኙ ተከልክለው በእስር መቆየታቸው ይታወቃል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ