አንድነት ምርጫ ቦርድ የጠየቀውን ማሻሻያዎች አሟልቶ አስገባ
ስሙን በሚመለከት ማሻሻያ ሳያደርግ ቦርዱ እንዲወስንለት ጠየቀ
Ethiopia Zare (ኀሙስ ሐምሌ 17 ቀን 2000 ዓ.ም. July 24, 2008)፦ ”አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ” ፓርቲ ለምርጫ ቦርድ ፈቃድ መጠየቂያ ማመልከቻ ካስገባ በኋላ፤ ባለፈው ሣምንት ኀሙስ ዕለት ምርጫ ቦርድ በጽ/ቤቱ በኩል አስር ነጥቦችን ዘርዝሮ ማሻሻያዎችና ለውጦች እንዲደረግባቸው ለፓርቲው በደብዳቤ አሳውቆ በነበረው መሠረት፣ ፓርቲው በዛሬው ዕለት በደብዳቤ ምላሽ መስጠቱን ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገለጹ።
የምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት ቦርዱ የፓርቲ ምዝገባውን ጥያቄ ከማየቱ በፊት መሻሻል አለባቸው፣ ማብራሪያ መሰጠት አለባቸው ካላቸው አስር ነጥቦች ውስጥ አንዱ ”አንድነት” የሚለው ስም የሰው ስም ስለሆነና ሕጉ ደግሞ ይህንን ስለማይፈቅድ ቃሉን መጠቀም እንደማይቻል መግለጹን የዛሬ ሣምንት ኀሙስ መዘገባችን አይዘነጋም። ፓርቲው በዛሬው ዕለት ለምርጫ ቦርድ አስገባው በተባለው በዚሁ ማሻሻያ ላይ የስሙን ጉዳይ በሚመለከት ቅያሬ እንደማያደርግና ቦርዱ ይሁንኑ እንዲያይለት መጠየቁን ምንጮቻችን ገልጸዋል።
አንድነት ለምርጫ ቦርድ በዛሬው ዕለት ባስገባው ደብዳቤ ላይ ”አንድነት” ፓርቲ የሚለውን ልንከለከል አይገባም፤ ”አንድነት” የሚለው ስም የአባት ስም እስከሌለውና ”አንድነት ፓርቲ” እስከተባለ ድረስ ሊገልጽና ሊያሳይ የሚችለው አብሮ መሆንን እንጂ የሰው ስም መሆኑ አይደለም በማለት በስሙ ጉዳይ ላይ ማስተካከያ ሳያደርግ ማስገባቱን ለመረዳት ችለናል።
ፓርቲው ”አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ” የሚለውን ሙሉ ስም ያልተከለከለ ሲሆን፣ የተከለከለውና ማሻሻያ እንዲያደርግ የምርጫ ቦርድ ጽ/ቤት የጠየቀው ፓርቲው መጀመሪያ ባስገባው የፈቃድ መጠየቂያ ማመልከቻ ላይ ”አንድነት ፓርቲ” እያለ ስሙን በአጭሩ መጥራቱን አስመልክቶ ነው።
በዚህ አጋጣሚ ውድ የኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ አንባብያን/ት ባለፈው ሣምንት ዘገባችን ላይ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሙሉ ስሙን ተከለከለ ብለን አለመዘገባችንንና ”አንድነት” የሚለውን ስም ብቻ መከልከሉን ስንዘግብ ስሙን ብቻ በትምህርተ ጥቅስ (ኮቴሽን) ውስጥ ስለተጻፈ ይገልጸዋል የሚል እምነት ነበረን። በትምህርተ ጥቅስ ውስጥ መቀመጡ በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ ገላጭ ሆኖ ባለመገኘቱና ብዥታን በመፍጠሩ በዚህ አጋጣሚ ይቅርታ እንጠይቃለን። ያለፈው ሣምንት ሙሉ ዘገባችንን በድጋሚ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ።
ከዚሁ ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲህ ጋር በተያያዘ፤ የፓርቲው ለሥራ አስፈጻሚ አባላቱ በደብረዘይት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ለሦስት ቀናት ያዘጋጀውን ሥልጠና በነገው ዕለት ይጀምራል። ሥልጠናው የሚካሄደው በሦስት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሲሆን አንደኛው ”የግጭት አፈታት”፣ ሁለተኛው ”ዕቅድ አዘገጃጀት”፣ ሦስተኛው ደግሞ ”የቡድን ምስረታና ግንባታ” የሚሉ መሆናቸው ታውቋል።



