ሦስት የቀይ መስቀል መድኃኒት ቤቶች በአዲስ አበባ ተዘጉ
Ethiopia Zare (ቅዳሜ ሐምሌ 19 ቀን 2000 ዓ.ም. July 26, 2008)፦ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር፣ በአዲስ አበባ የሚገኙ ሦስት የመድኃኒት መሸጫ መደብሮቹ ተዘጉ። የማኅበሩ መድኃኒት ቤቶች፣ የመድኃኒት ዋጋቸው ተመጣጣኝ መሆን ለተጠቃሚው ኅብረተሰብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክቱ እንደነበር ታውቋል።
ከማኅበሩ የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በአዲስ አበባ ቁጥር አንድ ፒያሳ፣ ቁጥር ሁለት ሳሪስ፣ ቁጥር ሦስት በየካ ክፍለ ከተማ፤ በአጠቃላይ ሦስት መድኃኒት ቤቶች የነበሩት ሲሆን፣ በአሁኑ ሰዓት ሦስቱም አገልግሎት መስጠት አቁመዋል።
ማኅበሩ ከሚያስተዳድራቸው ከእነዚህ ሦስት መድኃኒት ቤቶች ውስጥ ሳሪስ አካባቢ የሚገኘው፣ በመሸጫ ቤቱ ላይ መንገድ የሚወጣበት በመሆኑ ሲዘጋ፣ በፒያሳና በየካ ክፍለ ከተማ ያሉት ሁለት ቅርንጫፎቹ ደግሞ ባለሞያ ስለሌላቸው ተዘግተዋል። ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው፣ ለሦስቱ የማኅበሩ ፋርማሲዎች፣ ባለሙያ ለመቅጠር ከአምስት ጊዜ በላይ ማስታወቂያ የወጣ ሲሆን፣ ሊቀጠር የሚችል ግን አልተገኘም።
የመረጃ ምንጮቻችን በቀይ መስቀል መድኃኒት ቤቶች የሚቀጠር ባለሞያ ሊጠፋ የቻለበትን ምክንያት ሲገልፁ፣ የደሞዝ መጠናቸው ከገበያው ዋጋ እጅግ የተራራቀና አነስተኛ በመሆኑ ነው። በዚህም ምክንያት የተማሩ ፋርማሲስቶች በማኅበሩ መድኃኒት ቤቶች ለመቀጠር አይበረታቱም።
በሌላ በኩል ስለዚህ ጉዳይ የማኅበሩ ምንጮቻችን ሲያስረዱ፤ የቀይ መስቀል መድኃኒት ቤቶች ሱቆቻቸው ከቀበሌ የተሰጧቸውና መድኃኒትም የሚያስገቡት ከቀረጥ ነፃ በመሆኑ መድኃኒቶቹ በቅናሽ ዋጋ እንደሚሸጡ ነው።
እናም መድኃኒት ቤቶቹ ከሚያገኙት ትርፍ ላይ የባለሙያና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችን ደሞዝ ከፍለው ለማስተዳደር፣ ተቸግረው እንደነበር ያስረዳሉ።
በዚህም የተነሳ መድኃኒት ቤቶቹ ባለሙያ ስላልነበራቸው፣ የኢትዮጵያ መድኃኒትና ቁጥጥር ባለሥልጣን “ያለ ባለሙያ” ልትሠሩ አትችሉም በሚል እንደዘጋባቸው ታውቋል። ማኅበሩ የተዘጉትን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች 37 የመድኃኒት መደብሮች አሉት።
አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች እንዳሉትም፣ መድኃኒት ቤቶቹ ለረጅም ጊዜያት ተጠቃሚን በቅናሸ ዋጋ ከማገልገላቸውም በላይ፣ ገበያ ላይ የማይገኙ መድኃኒቶችን በማቅረብ ተመራጭነትን አግኝተዋል።
አሁንም ቢሆን መድኃኒት ቤቶቹ ያሉባቸውን ችግሮች አስወግደው ተጠቃሚውን ኅብረተሰብ ከበዝባዥ ነጋዴዎች ይታደጉ ዘንድ፣ የሚመለከተው አካል አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጥ ያነጋገርናቸው የመድኃኒት ተጠቃሚዎች ገልጸውልናል።