አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ያላትን ፖሊሲ የኦባማ ወይም የማኬይን መመረጥ እንደማይለውጠው ዴቪድ ክራመር ገለጹ
Ethiopia Zare (ማክሰኞ ሐምሌ 22 ቀን 2000 ዓ.ም. July 29, 2008)፦ በአሜሪካ ምርጫ ኦባማም ይመረጥ ማኬይን አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምታራምደው ፖሊሲ እንደማይቀየር የአሜሪካ የዲሞክራሲና ሰብዓዊ መብት ቢሮ ረዳት ሴክረታሪ ሚስተር ዴቪድ ክራመር ገለፁ። አያይዘውም ሀገራቸው በኢትዮጵያ ያለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ፣ ፕሬስንና መያዶችን አስመልክቶ የወጣው ሕግ እንደሚያሳስባት ተናግረዋል።
ሚስተር ክራመር በኢትዮጵያ ባደረጉት አጭር ጉብኝት፣ ጠ/ሚር መለስ ዜናዊን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችንና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን አነጋግረዋል።
ሚስተር ክራመር በኢትዮጵያ የሁለት ቀን ጉብኝታቸውን ካጠናቀቁበት ዕለት ኀሙስ ከሰዓት በኋላ በአሜሪካን ኢምባሲ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ በአሜሪካ ምርጫ ኦባማም ይመረጥ ማኬይን አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምታራምደው ፖሊሲ ሊቀየር እንደማይችል በመግለጽ ጥቆማ ሰጥተዋል።
አያይዘውም በኢትዮጵያ ያለው የሰብዓዊ መብት አያያዝና አጠባበቅ፣ በይበልጥ ደግሞ በቅርቡ የፕሬስና ኢንፎርሜሽን ነፃነትንና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን (መያዶችን) አስመልክቶ የወጣው ረቂቅ አዋጅ፣ መንግሥታቸውን በእጅጉ እንደሚያሳስበው በአጽንኦት ገልፀዋል።
ሚዲያ በየትኛውም ሀገር የዲሞክራሲ ግንባታ ሂደቱን እንደሚያጠናክር ገልፀው፣ በኢትዮጵያም ሚዲያው የበለጠ እንዲጠነክር እና እንዲያብብ የአሜሪካ መንግሥት ፍላጎት ነው ሲሉ አመልክተዋል።
እነዚህን ጉዳዮች አስመልክቶ ከጠ/ሚሩና ከሌሎች የመንግሥት አካላት ጋር ውይይት ያደረጉ መሆኑን የተናገሩት ክራመር፣ በመንግሥት በኩል ስለረቂቅ ሕጎቹ አስፈላጊነት መልስ ማግኘታቸውን ገልፀው፤ መልሶቹ ምን እንደሆኑ እና ምን ያህል አስፈላጊና አሳማኝ ስለመሆናቸው ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ማብራሪያ ሳይሰጡ ቀርተዋል።
የአሜሪካ መንግሥት ሽብርተኝነትን በመከላከልና የዲሞክራሲ ሥርዓትን በመገንባት ረገድ፣ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት እንደሚቀጥል ገልፀው፣ ኦባማ ይመረጡ ማኬይን የአሜሪካ መንግሥት ለኢትዮጵያ ያለውን ትኩረት እንደማይለውጠው ገልፀዋል። ከዚህ በተጨማሪ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ላይም ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ጋር አጭር ውይይት እንዳደረጉ ጠቅሰዋል።



