የአንድነት ፓርቲ ማመልከቻ ዓርብ በቦርዱ ይታያል
ቦርዱ በአንድ ወር ምላሽ ካልሰጠ ድርጅቱ ሕጋዊ ይሆናል
Ethiopia Zare (ኀሙስ ነኀሴ 1 ቀን 2000 ዓ.ም. August 07, 2008)፦ ዛሬ ከአዲስ አበባ በደረሰን መረጃ መሰረት አንድነት ፓርቲ አስር ማስተካከያዎችን አድርጎ ያስገባው ማመልከቻ ከጽሕፈት ቤቱ ወደ ቦርዱ መመራቱንና ዓርብ ለመጀመሪያ ጊዜ ቦርዱ እንደሚያየው ታወቀ።
የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት ማመልከቻው ለቦርዱ ከመቅረቡ በፊት የድርጅቱን የምሕጻረቃል ስም ‘አንድነት’ የሚለው የሰው ስም በመሆኑ ይቀየር የሚልና ሌሎች አስር ማስተካከያዎች እንዲደረጉ ጠይቆ የነበረ ሲሆን፣ አንድነት ፓርቲም የተጠየቀውን አሟልቶ ማስገባቱ ይታወቃል።
ተስተካክሎ ለጽሕፈት ቤቱ የገባው ማመልቸቻ ለቦርዱ ተላልፎ ነገ ዓርብ ቦርዱ አይቶ ውሳኔ እንደሚሰጥበት ምንጮቻችን አረጋግጠዋል።
በምርጫ ቦርድ ሕግ መሰረት አንድ ማመልከቻ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ምላሽ ካልተሰጠ ማመልከቻ አቅራቢው ድርጅት ሕጋዊ ይሆናል እንደሚል ይታወቃል።



