“እንዴት ወደኋላ ተመልሶ፣ ከትናንት ምሽት ጀምሮ የሚሠራ አዋጅ ይታወጃል?”

PM Hailemariam Desalegn

Ethiopia Zare (እሁድ መስከረም ፳፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. October 9, 2016)፦ ትናንት የሚኒስትሮች ምክር ቤትን በአስቸኳይ የሰበሰቡት ጠ/ሚ/ር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ምክር ቤቱን አባላት በማሳመን በሀገሪቱ ያለውን የህዝብ ተቃውሞና አለመረጋጋት ምክንያት በማድረግ ለስድስት ወር የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጃቸው ታወቀ። ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከትናንት ማምሻ ቅዳሜ መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ተፈጻሚነት እንደሚኖረው ለማወቅ ችለናል።

ላለፉት ተከታታይ አስር ወራት በተለይም በኦሮሚያ ክልል፣ እንዲሁም በአማራ እና በደቡብ ክልልሎች እየተቀጣጠሉ የሄዱትን ህዝባዊ እምቢተኝነት ተከትሎ በደረሰው የሰው ሕይወት መጥፋትና የንብረት መውደም ላይ የሚኒስትሮች ምክር ቤቱ መነጋገሩ ታውቋል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤቱ ለዚህ አዋጅ አስፈላጊነት የሰጠው ምክንያት፤ “ከውጭ ጠላቶች ጋር የተባበሩ ፀረ-ሠላም ኃይሎች የሀገሪቱን ሠላምና ፀጥታ ለማደፍረስ” የሚል መሆኑ ታውቋል። ጠ/ሚ/ር ኃይለማርያም ደሳለኝ የአስችኳይ ጊዜ አዋጁን አስፈላጊነት በተመለከተ ሲናግሩ፤ “የሀገራችንን ሕልውና አደጋ ውስጥ ወደሚያስገቡ ሁኔታዎች ሊቀየሩ እንደሚችሉ ስለምናምን፤ ህዝቡም እነዚህ ሁኔታዎች በዕለት ተዕለት ኑሮው ላይ ስጋቶች እየጫሩ እንደመጡ በስፋት እየገልጸና መንግሥት አስፈላጊውን እርምጃ በመውሰድ እነዚህን ነገሮች ማስተካከል አለበት የሚል ሰፊ የህዝብ ጥያቄና ግፊት በመኖሩ” አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጁን ገልጠዋል።

አስችኳይ የጊዜ አዋጁ ለህዝቡ በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የተገለጸው ዛሬ ጠዋት መሆኑ በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ ጥርጣሬን አጭሯል። እነዚሁ ወገኖች እንደሚያስታውሱት ከሆነ፣ ከዚህ ቀደም ወደኋላ ተመልሰው እንዲሠሩ ከተደረጉ ሕጎች ውስጥ ይኽኛው ሁለተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል። የመጀመሪያው በሚል ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጀምሮ ይሠራበት የነበረውን ሕግ ያፈረሰው፤ ”ባንክ ቤት የተፈራረሙት ውል፣ ውልና ማስረጃ እንደተፈራረሙት ውል ሕጋዊና በፍርድ ቤት ተቀባይነት ይኖረዋል” የሚለው ሕግ ሲወጣ ወደኋላ ሄዶ እንዲሠራ በማድረግ በጎጃሜዎች ተይዘው የነበሩትን እነጣና ትራንስፖርትን ጨምሮ በርካታ ንብረቶቻቸውን ንግድ ባንክ እንዲሸጥ ፈቃድ መሰጠቱን ያስታውሳሉ።

እነዚሁ ወገኖች አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ትናንትናውኑ ለህዝብ መገለጽ ሲገባው፣ እንዴት ወደኋላ ተመልሶ፣ ከትናንት ምሽት ጀምሮ የሚሠራ አዋጅ ይታወጃል በማለት ያላቸውን ጥርጣሬ ለኢትዮጵያ ዛሬ ገልጠዋል። በማከልም፤ ትናንት ማምሻውንና ሌሊት በመንግሥት ኃይሎች የተፈጸሙ ድርጊቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ያላቸውን ጥርጣሬ አልሸሸጉም።

ከዚህም ሌላ የአዋጁ ዝርዝር እስካሁን (ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ጊዜ ደረስ) አለመገለጹ በብዙዎች ዘንድ ጥርጣሬ መጫሩን ለመረዳት ችለናል።

ባለፉት ፳፭ ዓመታት ውስጥ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅ፤ ይህ ሁለተኛው ሲሆን፣ የመጀመሪያው ምርጫ ፺፯ትን ተከትሎ በቀድሞው ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ የታወጀው እንደሆነ ይታወሳል። ይህ ጊዜያዊ አስቸኳይ አዋጅ ተፈጻሚነቱ ለስድስት ወር ቢሆንም፤ ከዚያም ሊያጥር እንደሚችል ታውቋል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ