ለአለቃ አያሌው ታምሩ መታሰቢያ ድረ ገጽ ተከፈተ
Ethiopia Zare (ኀሙስ ነኀሴ 8 ቀን 2000 ዓ.ም. August 14, 2008)፦ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሊቃውንት ጉባዔ ዋና ሰብሳቢ ለነበሩት ለአለቃ አያሌው ታምሩ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ በማሰብና ሥራዎቻቸውን ለምዕመናን ለማቅረብ ሲባል በስማቸው ድረ ገጽ መከፈቱን ልጃቸው ወ/ሮ ጽዮን አያሌው ለኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ገለጸች።
ድረ ገጹ በፍልሰታ ጾም ለህዝብ ይፋ የሆነበትን ምክንያት ለኢትዮጵያ ዛሬ ስታስረዳ፤ አለቃ አያሌውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ምዕመናን የሚያውቋቸው ስለእመቤታችን ክብር ሲያስተምሩ በመሆኑና የፊታችን ረቡዕ ነኀሴ 14 ቀን 2000 ዓ.ም. ያረፉበትን የአንደኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ እንደሆነ ገልጻልናለች። (”አለቃ አያሌው ታምሩ” ድረ ገጽን ለመጎብኘት እዚህ ይጫኑ! http://www.aleqayalewtamiru.org )
ከዚህም ሌላ በኢትዮጵያ ውስጥ ”አያሌው ታምሩ ድርጅት” የሚባል ግብረሰናይ ድርጅት ለማቋቋም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ወ/ሮ ጽዮን አክላ ገልጻለች። የድርጅቱ የቅርብ ጊዜ ዓላማ በኢኮኖሚ ማነስ አብያተ ቤተክርስቲያናትና ገዳማት እንዳይዘጉ መርዳት ሲሆን፣ ከሩቅ ጊዜ ዓለማዎቹ ውስጥ ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስን ለዓለም ማስተዋወቅ፣ የኦርቶዶክስ ትምህርት እንዲስፋፋ ማድረግ፣ የግዕዝ ቋንቋ ት/ቤቶች እንዲከፈቱ ማድረግ፣ ካህናቶች በተለያዩ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ትምህርትን እንዲያስተምሩ ማገዝ፣ ... የመሳሰሉትን እንደሚገኙበት ወ/ሮ ጽዮን ለኢትዮጵያ ዛሬ ገልጻለች።
አለቃ አያሌው ታምሩ ከአባታቸው ከአቶ ታምሩ የተመኝና ከእናታቸው ከወይዘሮ አሞኘሽ አምባዬ፤ በጎጃም ክፍለ ሀገር በብቸና አውራጃ በእነማይ ወረዳ በታላቁ ደብር ወገዳም በደብረ ድማኅ ቅዱስ ጊዮርጊስ ልዩ ስሙ ቤተ ንጉሥ በተባለ ቦታ መጋቢት 23 ቀን 1915 ዓ.ም. በዕለተ ሆሣዕና ተወልደው፤ በ84 ዓመታቸው ነኀሴ 14 ቀን 1999 ዓ.ም. ማረፋቸው ይታወቃል። አለቃ አያሌው የ14 ልጆች አባት ነበሩ።
የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው ነሐሴ 17 ቀን 1999 ዓ.ም. ለረዥም ዓመታት ባገለገሉበት የአዲስ አበባው ደብረ አሚን ተክለኃይማኖት ቤተ ክርስቲያን በርካታ ህዝብ በተገኘበት የተፈፀመ ሲሆን፣ ቤተሰቦቻቸው በደብሩ የመታሰቢያ ኃውልትና የጸሎት ቤት ለማሠራት እንዲፈቀድላቸው ከነኀሴ 29 ቀን 1999 ዓ.ም. ጀምሮ ጥያቄ ቢያቀርቡም ከቤተክርስቲያኗ መልካም ምላሽ እንዳላገኙና ጥያቄያቸውን ለደብሩ ብቻ ሳይሆን ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤትና ለፓትርያኩ ለማቅረብ ቢሞክሩም መፍትሄ እንዳልተሰጣቸው የካቲት 2 ቀን 2000 ዓ.ም. ማስነበባችን አይዘነጋም። የመታሰቢያ ኃውልቱን ለመሥራት እስካሁን ድረስ ፈቃድ እንዳልተገኛ ወ/ሮ ጽዮን አረጋግጣልናለች።
አለቃ አያሌው የተለያዩ የኃይማኖት መጻሕፍትን ያሳተሙ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ ዓይነ ሥውራን ማኅበር መሥራቾች አንዱ የነበሩና፤ መጀመሪያ የማኅበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት ኋላም የቦርድ ሊቀመንበር በመሆን አገልግለዋል።
የቤተ ክርስቲያኒቱ የሊቃውንት ጉባዔ ዋና ሰብሳቢ በነበሩበት ወቅት ”የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት፣ ትምህርት፣ ሥርዓትና አስተዳደር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተለወጠና እየተበላሸ ሄዷልና ጥፋቱ ይታረም” በማለት አቤቱታና ተማጽኖ ሲያሰሙ ስለነበር ከ50 ዓመት በላይ ካገለገሉበት የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ያለምንም ጡረታ ከሥራ ገበታቸው ሚያዝያ 1988 ዓ.ም. መገለላቸው አይዘነጋም።
አለቃ አያሌው አቡነ ጳውሎስንና ተከታይ ጳጳሳትን፣ እንዲሁም የአቡነ ጳውሎስ ስም በቅዳሴ ጊዜ እንዳይጠራም ማውገዛቸው አይዘነጋም።



