The vintage planes had taken off from Sudan for the three-hour flight into Ethiopia

ኢትዮጵያ ዛሬ (ዓርብ ኅዳር ፲፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. Nov. 25, 2016)፦ ትናንት የአየር ንብረቴን በሕገ ወጥ መንገድ ሲያቋርጡ ያዝኳቸው ያላቸውን 20 ቀላል አውሮፕላኖችንና በውስጡ የሚገኙ 42 የተለያዩ ሀገራት ዜጎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የተናገረው መንግሥት አሁን እንደለቀቃቸው ይፋ አድርጓል።

የቢቢሲ ዘገባ እንደሚያመለክተው ሰዎቹ ሊለቀቁ የቻሉት ከዲፕሎማቶች በደረሰበት ጫና ነው።

አብራሪዎቹ ባለፈው ኅዳር ፲፫ (ኖቬምበር 22) ከግሪክ የተነሱ ሲሆን፤ ጉዟቸው ወደ ደቡብ አፍሪካዋ ከተማ ኬፕታውን ነበር። በዚህም በሱዳን የአየር ክልል አልፈው ኢትዮጵያን በማቋረጥ ላይ ሳሉ ነው በጋምቤላ አየር ማረፊያ እንዲያርፉ የተደረጉት።

ይሁን እንጂ ሰዎቹ ከአየር ክልል ከጠፉ በኋላ አድራሻቸው ሳይገለጽ ለሰዓታት የቆየ ሲሆን፣ አርፍዶም ቢሆን የኢትዮጵያ መንግሥት በእጁ እንደሚገኙ ለዓለማቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ገልጿል።

በኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ቁጥጥር ስር ከዋሉት አብራሪዎች ውስጥ የ፸፩ ዓመት የዕድሜ ባለፀጋው እንግሊዛዊው ማውሪስ ኪርክ የሚገኝበት ሲሆን፣ ያበራት የነበረችው ”1943 Piper Cub” የተሰኘችው እ.ኤ.አ. ከ1937 እስከ 1947 በፓይፐር ኤርክራፍት የተገነባች መሆንዋ ታውቋል። እንደ ዘ ጋርድያን ጋዜጣ ዘገባ ከሆነ ከአርባ ሰዎች በላይ ኢትዮጵያ አግታ ነበር።

በሌላ ዘገባ ዌስት ፕሌይንስ ዳይሊ ሜል፤ “ቪንታዥ ኤር ራሊ” በሚል መጠሪያ የሚዘጋጅ ውድድር ሲሆን፣ ከግሪኳ ክሬቴ ደሴት ወደ ደቡብ አፍሪካዋ ኬፕታውን የሚደረግ በረራ ነበር። በራሊው የሚሳተፉት አውሮፕላኖች በሃያኛው ክፍለዘመን መጀመሪያ ላይ የተሠሩ መሆናቸው ታውቋል። ራሊው አስር አገሮችን የሚያዳርስ ሲሆን፣ ፴፯ (37) ከተሞች ላይ በማረፍ በ፴፭ (35) ቀናት የሚጠናቀቅ ነበር።

ጉዳዩ ይፋ ከሆነ በኋላ የእንግሊዝ፣ የአውስትራሊያና የአሜሪካ ዲፕሎማቶች በፍጥነት ከመንግሥት ጋር ውይይት ማድረጋቸው የተገለጸ ሲሆን፤ በዚህም ሳቢያ ሰዎቹ ያለምንም ተጨማሪ ውንጀላ ወይም ምርመራ በነጻ እንዲለቀቁ ተደርጓል።

በሕገ ወጥ መንገድ ድንበሬን ጥሰው ገቡ ሲል በቁጥጥር ስር ያዋላቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ግን አሁን ለመለቀቃቸው ምንም የሰጠው ምክንያት ወይም ማስተባበያ የለም።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ