እስራኤል ፈላሻ ሙራዎችን መውሰድ አቆመች
Ethiopia Zare (ኀሙስ ነኀሴ 8 ቀን 2000 ዓ.ም. August 14, 2008)፦ እስራኤል ላለፉት 30 ዓመታት ከኢትዮጵያ ፈላሻዎችን ወደ ሀገሯ ማጓጓዝ እንዳቆመች ታወቀ። በእስራኤል የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አይሁዶች የእስራኤል መንግሥት የወሰደውን እርምጃ ተቃውመዋል።
የእስራኤል መንግሥት ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት አንድ መቶ ሃያ ሺህ ፈላሻ ሙራዎችን ከኢትዮጵያ የወሰደ ሲሆን፣ ባለፈው ማክሰኞ ሐምሌ 29 ቀን 2000 ዓ.ም. (August 5) ”የመጨረሻ” ያላቸውን 65 ፈላሻዎች ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል አጓጉዟል። የእስራኤልን መንግሥት እርምጃ ተቃውሞ የገጠመው ወደ እስራኤል ያልተወሰዱ 8,700 አካባቢ የሚሆኑ ፈላሻዎች ጎንደር ውስጥ ስለሚገኙ መሆኑ ታውቋል።
በ2003 እ.ኤ.አ. የእስራኤል ካቢኔ ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል የሚጓዙት የፈላሻ ሙራዎችን ቁጥር 17 ሺህ እንዲሆን በወሰነው መሠረት የመጨረሻዎቹ 65ቱ ፈላሻዎች መሆናቸውን የእስራኤል መንግሥት ቃል አቀባይ ገልጾ፣ የእስራኤል ቀጣይ ዓላማ በእስራኤል የሚገኙ የኢትዮጵያ ፈላሻ ሙራዎችን ሕይወት እንዲሻሻል ተጨማሪ ገንዘብ ማውጣት ነው ብሏል።
ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል ለመጓዝ የሚፈልጉ ፈላሻ ሙራዎች በቤተሰባዊ ግንኙነት፣ በሰብዓዊ ጉዳዮች እና በግል ጉዳዮች መታየታቸውን እንደሚቀጥሉ፤ ነገር ግን በጋራ እንደቀድሞው እንደማይታይ ለመረዳት ተችሏል።
”ፈላሻ ሙራዎችን የሚያጓጓዝ ፕሮጀክት መዘጋቱ መቻሉ ያጠራጠረኛል፤ ምክንያቱም በኢትዮጵያ የቀሩት የፈላሻ ሙራዎች ጉዳይ መጨረሻው መታወቅ ይኖርበታል” በማለት በእስራኤል ገዢ በሆነው የካዲማ ፓርቲ ውስጥ የሕግ ባለሙያ የሆነው ፈላሻ ሙራ ሻሎም ሙሉ ገልጿል።
ይህንን የእስራኤል መንግሥት ውሳኔ በተለያዩ ዓለማት የሚገኙ ጽዮናውያን እየተነታረኩበትና እየተከራከሩበት የሚገኙ ሲሆን፣ ውሳኔውን የሚቃወሙት እንደመኖራቸው መጠን የሚደግፉትም እንዳሉ ታውቋል።



