ሀብታሙ አያሌው፣ የሽዋስ አሰፋ እና አብርሃም ሰለሞን በነጻ ሲሰናበቱ፤ ዳንኤል ሺበሺ እና አብርሃ ደስታ ተከላከሉ ተባሉ

Ene Abraha Desta

ከፍተኛ ፍርድ ቤት በነፃ ባሰናበታቸው አምስት ተከሳሾች (ሀብታሙ አያሌው፣ ዳንኤል ሺበሺ፣ አብርሃ ደስታ፣ የሽዋስ አሰፋ እና አብርሃም ሰለሞን) ላይ አቃቢ ሕግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ብሎ ዓመት ከሦስት ወር በላይ በቀጠሮ ሲራዘም የነበረው ጉዳይ ዓርብ ኅዳር ፳፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. (Dec. 2, 2016) ብይን ተሰጥቶበታል።

ዳኞች በአራቱ ተከሳሾች ላይ ማለትም፤ ሀብታሙ አያሌው፣ ዳንኤል ሺበሺ፣ አብርሃ ደስታ እና የሽዋስ አሰፋ ላይ ከደህንነት መስሪያ ቤት የቀረበባቸውን የሽብርተኛ ድርጅት አባል ከሆኑ ግለሰቦች ጋር ያደረጉትን የስልክ ልውውጥ በመርመር ነው ውሳኔ የሰጡት። በዚህም መሰረት ሀብታሙ አያሌው ያደረጋቸው የስልክ ልውውጦች ሲታዩ በሽብርተኛ ድርጅት የተፈረጁ ድርጅቶች አባላት ጋር የተደረገ ቢሆንም፤ “በሰላማዊ መንገድ ሁኔታዎችን ለመለወጥ እና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ስለመገንባት” የሚያወሩ በመሆኑ የበታች ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ትክክል ነው ብለው በነፃ እንዲሰናበት ወስነዋል።

ዳንኤል ሺበሺ እና አብርሃ ደስታ ከፋሲል የኔአለም ጋር ያደረጉት የስልክ ልውውጥ ሲታይ በክሱ እንደቀረበው የሽብር ተግባር ሊፈፅሙ ባያቅዱም፤ በሽብርተኛ ድርጅት ከተፈረጀው ግንቦት 7 ጋር ሁለገብ ትግል በሚለው ሃሳብ የመስማማት አዝማሚያ እንዳላቸው እና ከሰላማዊ ትግል ባለፈ የመንቀሳቀስ ፍላጎት እንዳላቸው እንደሚያሳይ ዳኞቹ ገልፀዋል። ስለሆነም የፀረ ሽብር አዋጁ አንቀፅ 7(1)ን የእንዲከላከሉ ሲሉ ብይን ሰጥተዋል።

የሽዋስ አሰፋም እንዲሁ ከፋሲል የኔአለም ጋር ያደረገውን የስልክ ምልልስ እንዳዩት የገለፁት ዳኞቹ፤ የሽብር ድርጊት ለመፈፀምም ሆነ በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳለው ስለማያሳይ በነፃ እንዲሰናበት ተበይኗል።

አብርሃም ሰለሞንን በተመለከተ የቀረበ የተጠለፈ የስልክ ልውውጥ ከደህንነት የቀረበ ሪፓርት ስላልነበረ፤ በቀረቡት የአቃቢ ሕግ ምስክሮችን መሰረት አድርገው ነው ዳኞች ውሳኔውን የሰጡት። ከአቃቤ ሕግ ምስክሮች ተከሳሹ በመንግሥት ላይ ያለውን ጥላቻ እና በግንቦት 7 እየተሳበ መምጣቱን መመልከት ይቻላል፤ ሆኖም ግን በአባልነት ስለመመልመሉ እና ስለተሳትፎው የተገለፀ ነገር ባለመኖሩ በነፃ እንዲሰናበት ወስኗል።

161202

በዛሬው ችሎት ላለፉት በርካታ ጊዜያት በሕመም ምክንያት ችሎት ሳይቀርብ በተወካዩ አማካኝነት ጉዳዩን ሲከታተል የነበረው ሀብታሙ አያሌው ከሕመሙ በመጠኑ አገግሞ በችሎት የተገኘ ሲሆን፤ አብርሃ ደስታ ደግሞ እዛው መቀሌ የሚገኝ ፍርድ ቤት በፕላዝማ ችሎቱን ተከታትሏል። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጥሰሃል በሚል በእስር የሚገኘው ዳንኤል ሺበሺ ችሎት ሳይቀርብ ቀርቷል።

በፀረሽብር አዋጁ አንቀፅ 7(1) እንዲከላከሉ የተበየነባቸው አብርሃ ደስታ እና ዳንኤል ሺበሺ፤ ክሳቸውን አቃቤ ሕግ ሲያንቀሳቅስ እና መጥሪያ ከደረሳቸው በኋላ በድጋሚ ወደ እስር ቤት ተመልሰው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጉዳያቸውን መከታተል እንደሚጀምሩ ይጠበቃል።

ምንጭ፡ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ፕሮጄክት

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ