”ከማቀርበው ይግባኝ ትክክለኛ ፍትህ እጠብቃለሁ” ካሊድ አደም
Ethiopia Zare (እሁድ ነኀሴ 11 ቀን 2000 ዓ.ም. August 17, 2008)፦ ”ልጅህን በመቀስ ገርዘሃል” ተብሎ ማርች 28 ቀን 2003 እ.ኤ.አ. በቁጥጥር ስር ውሎ፣ አፕሪል 4 ቀን 2004 እ.ኤ.አ. በ50 ሺህ ዶላር ዋስትና ተለቅቆ ጉዳዩን በፍርድ ቤት ሲከታተል ከቆየ በኋላ ኖቨምበር 2 ቀን 2006 እ.ኤ.አ. የ10 ዓመት ጽኑ እስራት የተፈረደበት ነዋሪነቱ በጆርጂያ ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ ኤሜሪካ የሆነው ካሊድ አደም ”ከማይቀርበው ይግባኝ ትክክለኛ ፍትህ እጠብቃለሁ” ሲል ሰሞኑን ደብዳቤ መጻፉ ታወቀ። ሙሉ የደብዳቤው ቃል እንደሚከተለው ይገኛል።
ልጅህን በመቀስ ገርዘሃል በማለት ልብ ወለድ ክስ ተመስርቶብኝ በዚሁ ክስ በጥፋተኝነት የ10 ዓመት ጽኑ እስራት ከተፈረደብኝ ሁለት ዓመት ሊሆን ጥቂት ወራቶች ቀርተውታል። ይህንንም የሀሰት ክስ ይግባኝ በማለት ባልሰራሁትና በማላውቀው ወንጀል በእስር ላይ እገኛለሁ። የተመሰረተብኝ የሀሰት ክስ በተለያዩ የዓለም አቀፍና የኢትዮጵያ ሚዲያዎች የተዘገበ መሆኑን ባውቅም፤ እንኳን ክሱን ለሰማው ሰው ቀርቶ ለኔው፤ የተመሰረተብኝ ክስ ከፍተኛ አስገራሚ ነገር ሆኖ የህሊና ቅዠት ፈጥሮብኛል። በሕይወቴ ሲደረግ አይቼ የማላቀውን ተግባር እንዴት? በምን ሁኔት አድርገዋለሁ? ይህንን ድርጊት ክሱ እንደሚለው ማንም ሳያይ ሳይታወቅ ሁለት ዓመት እንዴት ሊቆይ ይችላል? በየትኛው የመረጃ ሚዛን ጥፋተኛ ሆኜ ተገኘሁ? በአሉ አሉ ክስ መመስረት፣ ሰውን በሀሰት ለከፍተኛ እስራት መዳረግ፣ የአንድን ሀገር ስም በጅምላ በዓለም ላይ ማጥፋት በወንጀለኝነት አይቆጠርምን?
የሕግ መዋቅሩን ከፍተኛ ድክመት በማጤን ይህን ሁሉ በማቀናበር ክስ የመሰረቱት በጥላቻ የተሞሉት የቀድሞ ባለቤትና ቤተሰቧ ይህንን ወንጀል ሰርተው፣ የሕግ ከለላ ማግኘታቸው ነገሩን የበለጠ ኢ-ፍትሃዊ ያደርገዋል።
ከሳሾቼ የሀሰቱን ክስ መንደርደሪያ ያደረጉበት መሰረት ”የኢትዮጵያ ባህል” ስለሆነ በማለት ነው። ለመሆኑ በየትኛው የኢትዮጵያ ታሪክና ባህል ነው፤ ወንድ ልጅ የገዛ ሴት ልጁን በመቀስ የገረዘው? በየትኛው የዓለም ታሪክ ነው እናት የልጇን ግርዛት ሳታውቅ ሁለት ዓመት የቆየችው? ይህንን ድርጊት በድብቅ ማድረግና እንዳይታወቅ የማድበስበስ ችሎታስ ከየት ይገኛል?
ይህንንስ ለልጄ በዚህ ዘመን እንዴትስ እመኛለሁ? ኢትዮጵያዊ መሆን በራሱ የሴት ግርዛት ባህል ተከታይ ሊያስብል ይችላልን? ይህን በመረጃነት ማቅረብ ለእስራት ይዳርጋልን?
ይህንን ክስ የመሰረቱት የቀድሞ ባለቤትና ቤተሰቦች በድንገትና ያለምክንያት አይደለም።ለዓመታት በነበረው ፍቺና በፍቺው ምክንያት በተፈጠረው የአሳዳጊነት (የልጄን) መብት በመከራከር ላይ ባለንበት ወቅት ነበር። የነበረው ሕግ እንደሚለው ”ማንኛውም አባት ወይም እናት ያሳዳጊነት፣ በግልም ይሁን በተናጥል ወይም በሀገር ክፍፍል መጠየቅ መብታቸው ነው። ይህ መብት ሊናድ የሚችለው አባት ወይም እናት ለልጆቻቸው አደጋ ሆነው ሲገኙና ሲረጋገጥ ነው።” የሚለውን የሕግ አንቀፅ መጠቀም ብልሀት ብለው ይህንን ክስ አስበውበታል፣ ተቀምጠው ተነጋግረውበታል እንዴት? በምን አይነት? ፍርድ ቤትን፣ ዓቃቤ ሕግን ማሳመን እንደሚችሉ በደንብ አጢነዋል።
በኢትዮጵያ ይህ ባህል ስለመኖሩና የኔ ኢትዮጵያዊነት ለሚያቀርቡት የሀሰት ክስ ተዓማኒነት ይፈጥራል የሚል እርግጠኛ አስተሳሰብ አድሮባቸዋል። መቼ ተደረገ? በምን ሁኔታ? ለሚለው ግን ፍርድ ቤቱንና ዓቃቤ ሕጉን በማድረጋቸው ያለሙትን ግብ እንደሚፈልጉት እንዳቀዱት አግኝተዋል። ለኔ ግን ይህ ልብ ወለድ ክስና ፍርድ ቤት ይህንን ተመርኩዞ ያደረገው ኢ-ፍትሃዊ ውሳኔ የባሰ ግር አሰኝቶኛል።
ይህንን ጉዳይ በጽኑ ለመከራከር የተከሳሽ ምስካሪ ሆነው ለፍርድ ቤቱና ከዛም ውጭ ለጆርጂያ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ቃላቸውን የሰጡት የሴቶች መብት ድርጅት መስራችና ሴት ግርዛት ኤክስፐር የሆኑት ግሎሪ ኪላንኮ (Glory Kilanko) ”በሴቶች ግርዛት ላይ ለ20 ዓመት ጥናት አድርጌያለው፣ በራሴም ላይ ደርሷል፣ የኢትዮጵያንም ሆነ የአፍሪካን ታሪክ በደንብ አውቃለሁ፤ በአፍሪካም ሀገሮችም ሄጄ ጥናት አካሂጃለሁ፣ ለተባበሩት መንግሥታት በሴቶች መብቶች ላይ በዚህ ጉዳይ 15 ሰዎች ጥናት አቅርበናል። አንደኛ፡- በባህል ደረጃ ራሱ በኢትዮጵያ ታሪክ ወንድ ልጅ አይገርዝም፣ ማየት ራሱ አይፈቀድለትም ወይም እንደነውር ይቆጠራል። ሁለተኛ፡- ግርዛት ለማካሄድ በራሱ ከአራት ሰው በላይ ይስፈልጋል፣ ሦስተኛ፡- ይህ ነገር በራሴ ደርሶ ሕመምና ስቃዩ ለቀናት መራመድ ሁሉ እንዳልችል አድርጎኛል። በተጨማሪም አንድ ልጇን ዕለት ተዕለት የምትንከባከብ እናት ይቅርና ሌላም ሰው በቤት ውስጥ የሚገኝ የልጅቷን ስቃይ ማየትና መመልከት ይችላል። ሕመሙ ከባሰም ለሞት ይዳርጋል። ይህ ድርጊት ሳይታወቅ ሁለት ዓመት ቆየ ማለቱ በራሱ የሚገርምና የአጠቃላይ ክሱ ራሱ ተዓምር ነው” በማለት እንባ እየተናነቃቸው ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።
ከዚህም ጎን በጉዳዩ የስድስት ወር ምርመራ ያደረጉ በፍቺው ፍርድ ቤት የተመደቡት ጆኣን ኮሊንስ (Mrs. Joann Collin) የተባሉ ሴት መቅረብና ለማስረዳት ቢፈልጉም ፍርድ ቤቱ እንዳይቀርቡ አድርጓል። ከዚህም ውጭ የነበሩትን ሰባት ምስክሮች አግዷል። የተለያዩ የመረጃ ዶክመንቶችም እንዳይቀርቡና እንዳይሰሙ ተደርገዋል። ’አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም’ እንደሚባለው ይህ የልብ ወለድና የሀሰት ክስ በዓለም የዜና ማሰራጫ መሽከርከር ጀምሮ ፍርድ ቤቱን፣ ዓቃቤ ሕጉን በግድና በኃይል፤ ሀሰት እውነት እንዲመስል ሕግ ገፍተዋል፣ ተከሳሽነት መሰረታዊ መብቴን በኃይል ገፈዋል ለእስርም ዳርገውኛል።
አሁንም ይህን ክስ ሀሰት ስለመሆኑና የተሠራውን ኢ-ፍትሃዊ ሂደት ለማቃናት ይግባኝ ጠይቄያለሁ። ኢትዮጵያውያን ድርጊቱ በራሳቸው ላይ እንደደረሰ በመቁጠር ዕለት ተዕለት ጉዳዩን በመከታተል፣ በዚህ ሀገር ታዋቂ ናቸው የሚባሉትን ጠበቆች ይዘዋል። የዚህ ክስ እውነትነትን ለማወቅ ያን ያህል ባያስቸግርም፣ ጠበቆቹም ይህንን ጉዳይ ይዘው በፍርድ ቤት ገብተው ፍትህን ለመጠየቅ ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል።
ሁኔታው ተድበስብሶ እንዲቀርና የተሠራው ኢ-ፍትሃዊ የሕግ ሂደት እንዳይጋለጥ ፍርድ ቤቱና ዓቃቤ ሕጉ በሚቻላቸው ኃይል መታገላቸው ከወዲሁ መገመት አያዳግትም። ይሁንና ይህን የፍርድ አካል ሕጉ በሚፈቅደው መሰረት ስለ ሀቅ እንዲቆም በፍትሃዊ ሂደት ጉዳይ ሕግ በሚያዘው መሰረት እንዲታይ ጠበቆቹ እየተዘጋጁ ይገኛሉ።
እኔም በዚህ በማላውቀውና ባላደረኩት ነገር ከተጣለብኝ የቅጣት እስር የምወጣበትን፣ በልጄ ላይ ከተደረገው የሀሰት ድርጊት ባሻገር በኔ ላይ ሌላ ወንጀል መፈጸም በራሱ በወንጀል ላይ ወንጀል እንዲፈጽሙ የተረማመዱበት ሕግ መንገዱ እንዲቆምና፣ የዚህ ሴራ ጠንሳሾች በራሳቸው የተቀናጀ ሴራ ቢተማመኑም ከሕግ በላይ እንደማይሆኑ የማይበትን ቀን እጠብቃለው። እስካሁን ስለፍትህ ከኔና ከቤተሰቦቼ ጋር በጽናት ለቆማችሁ፣ እየደከማችሁ ላላችሁ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ልባዊ ምስጋዬ ዘላለማዊ ነው።



