የከፍተኛ ፍርድ ቤት መዝገብ ቤት ኃላፊ በጉቦ ቅሌት ታሠሩ
‘በኢትዮጵያ ጉቦ ህጋዊ ይመስላል’ አስተያየት ሰጭዎች
Ethiopia Zare (እሁድ ነኀሴ 18 ቀን 2000 ዓ.ም. August 24, 2008)፦ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የአስተዳደር ክፍል፣ የመዝገብ ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ታዬ ተኮላ፣ ለልምምድ (አፓረንትሺፕ) ከመጣ ተማሪ ላይ 200 ብር ጉቦ ሲቀበሉ፣ እጅ ከፍንጅ ተይዘው የልደታ ክፍለ ከተማ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር አውሏቸዋል።
ዕድሜያቸው 50 ዓመት የሚጠጋና 30 ለሚሆኑ ዓመታት፣ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዳገለገሉ የሚነገረው አቶ ተኮላ፣ ከትናንት በስቲያ በቁጥጥር ስር ያዋላቸው የልደታ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መረጃ እንደሚያስረዳው፣ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ የፍተሻ ሠራተኛ ከሆነውና አቶ አብዲ ሱልጣን ከተባለ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የማታው ክፍለ ጊዜ የሕግ ተማሪ ጉቦ በመቀበላቸው ነው።
ዩኒቨርስቲው የሕግ ተማሪውን የመለማመጃ ጊዜ (አፓረንትሺፕ) በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይመድበውና፣ ይህንኑ ለማመልከት ወደ ቦታው ሲሄድ፣ የመዝገብ ቤት ኃላፊውን አቶ ታዬ ተኮላን አግኝቶ እንዳነጋግራቸው በሰጠው ቃል ገልጿል።
አቶ ታዬ በበኩላቸው፣ ስድስት የሕግ ተማሪዎች ልምምድ ላይ በመሆናቸው ቦታ እንደሌለ፣ ነገር ግን ቦታ የሚገኝ ከሆነ ስልክ እንደሚደውሉለት በመግለጽ፣ ስልኩን እንደተቀበሉት ተማሪው ለፖሊስ በሰጠው ቃል አስረድቷል።
በማግሥቱም በተቀበሉት ስልክ ደውለው፣ የተመደበበትን ወረቀት ይዞ እንዲመጣና፣ ሳይለማመድ እንደተለማመደ አድርገው ማስረጃ እንደሚሠሩለት በመግለጽ፣ ለምሣ የሚሆን ገንዘብ ስጠኝ ብለው እንደጠየቁትና እርሱም “ገንዘብ ስላልያዝኩ ነገ እንገናኝ” በሚል ረቡዕ ነኀሴ 14 ቀን 2000 ዓ.ም.፣ ሜክሲኮ ቅድስተ ማርያም ኮሌጅ ፊት ለፊት ካሉ ካፍቴሪያዎች በአንዱ እንዲገናኙ ቀጠሮ እንደሰጣቸውና ይህንን ጉዳይ ለልደታ ፖሊስ ጣቢያ ያስመዘግባል።
እናም ቁጥራቸው ኤምስ132175 እና ኤጂ2605070 የሆኑ ሁለት ባለመቶ ብሮችን በማስመዝገብ፣ ሲቪል የለበሱ ሁለት ፖሊስና አንድ የደህንነት ሠራተኛ በማስከተል ተማሪ አብዲ፣ አቶ ተኮላ ወደቀጠሩት ቦታ አምርቷል።
አብዲ የተጠቀሰውን ቁጥር የያዙትን ሁለት ባለ መቶ ብር ኖቶች ከሰጠና፣ አቶ ተኮላም ከተቀበሉ በኋላ ወዲያውኑ በቁጥጥር ስር ውለው፣ ልደታ ፖሊስ ጣቢያ ታስረዋል።
በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ከአሁን ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁናቴ የጉቦ ቅብብሎሽ የተበራከተ ሲሆን ጉዳይን ለማስፈጸም ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጉቦ መሸጎጥ የተለመደ ከመሆኑም በላይ ህጋዊ ሆኖ የሚሰራበት ይመስላል ሲሉ አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች ይተቻሉ።


