ከ66 ሰዎች በላይ ታስረዋል፣ እነሱን ለማስፈታት 20 ሽማግሌዎች አዲስ አበባ ናቸው

Abdulekerim, age 15, lost his right arm on Butajira conflictEthiopia Zare (ኀሙስ መስከረም ፩ (1) ቀን ፳፻፩ (2001) ዓ.ም. September 11, 2008)፦ በቡታጅራ ከተማ በተነሳው ብጥብጥ ቀኝ እጁን ያጣው አብዱልከሪም የተባለው የ15 ዓመት ታዳጊ ወጣት ”ነኀሴ 2 ቀን 2000 ዓ.ም. ከቤቴ ወጥቼ ወደ አያቴ ቤት ስዔድ፣ በድንገት ቀኝ እጄን በጥይት ተመታሁ። ሐኪም ቤት በሄድኩ ሰዓት አደጋው ከፍተኛ ስለሆነ፣ እጅህን መቆረጥ አለብህ ተባልኩና አደጋው በደረሰብኝ ማግስት በቡታጅራ ሆስፒታል ተቆረጥኩ” ብሏል።

 

ነኀሴ 2 ቀን 2000 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ከአዲስ አበባ 148 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ቡታጅራ ከተማ ከወረዳ ስያሜ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ረብሻ መነሳቱንና 12 ሰዎች መታሰራቸውን ነኀሴ 4 ቀን መዘገባችን አይዘነጋም። የታሰሩት ሰዎች ቁጥር 66 የደረሰ ሲሆን፣የከተማው ነዋሪዎች እስሩና እንግልቱ ሲበዛባቸው ሃያ የሚሆኑ የወረዳው አዛውንቶችን በማሰባሰብና በመወከል ወደ አዲስ አበባ አቤቱታቸውን ለማዕከላዊ መንግሥት፣ ለኢትዮጵያ ህዝብና ለመገናኛ ብዙኀን እንዲያሰሙላቸው ልከዋቸዋል።

 

አንዲት ስሟ እንዳይገለጽ የፈለገች ወ/ሮ በስያሜ ምክንያት በተፈጠረ አለመግባባት ሦስት ወንድሞችዋ እንደታሰሩ ገልጻ፤ ፖሊስ የጊዜ ቀጠሮ በመጠየቁ የዋስትና መብት ሳይሰጣቸው ከአንድ ወር በላይ በእስር እንደሚገኙ ገልጻለች።

 

የረብሻው መንስዔ 41 ቀበሌዎችን ያቀፈው ”መስቃን” ወረዳና አንድ ቀበሌ ገበሬ ማኅበርን የያዘው ”ዶቢ” ቀበሌ ተቀላቅለው፣ ”መስቃን ዶቢ” ይባሉ በሚል የከተማው አስተዳዳሪዎች ተፈፃሚ እንዲሆን ሲጠይቁ ውሳኔውን ባልተቀበሉት ነዋሪዎች መካከል የተፈጠረ አለመግባባት ነው።

 

የ”መስቃን” ወረዳ ህዝብ ስያሜው የተሰጠው ከ100 ዓመታት በፊት መሆኑና 41 ቀበሌዎችን የያዘ ወረዳ ሆኖ እያለ አንድ ቀበሌ እኩል ስያሜ እንዲያገኝ መወሰኑን የማይቀበሉ እንደሆነ ነዋሪዎቹ ይገልፃሉ።

 

ከወረዳው አስተዳዳሪዎችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በተደረገ ስብሰባም ”መስቃን” ብቻ ይባል በሚል ተወስኖ እያለ፣ በጎን ”መስቃን ዶቢ” በሚል ሊወሰን መሆኑ ነዋሪው በደረሰው መረጃ መሠረት፣ አለመግባባቱ ተፈጥሮ በተነሳው ረብሻ የሀገር ሽማግሌዎችን ጨምሮ ከ66 በላይ ሰዎች መታሰራቸውን ገልፀዋል።

 

ጉዳዩንም በሚመለከት የፌደራል ፖሊስ ገብቶ እንዲዳኛቸው ለማድረግ ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ለዕንባ ጠባቂ ተቋምና በመጨረሻም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት አቤቱታቸውን ማቅረባቸውን ይገልፃሉ።

 

የዕንባ ጠባቂ ተቋም የደረሰውን አቤቱታ መሠረት በማድረግ፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ምርጫ ከተካሄደ በኋላ የመስቃን ወረዳና የቡታጅራ ከተማ ምክር ቤቶች እስከ ዛሬ ድረስ ለምን ሊመሠረቱ እንዳልቻሉ እንዲገልጹለት በደብዳቤ ጠይቋል።

 

በሌላ በኩል 66 እስረኞች በፊርማቸው ለቡታጅራ አካባቢ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዋስ መብታቸው ተጠብቆ እንዲፈቱ ቢጠይቁም ”እስረኞቹ እንኳን ሊፈቱ በላይ በላዩ ተጨማሪ ሰዎች እየታሰሩ ነው” ሲሉ ነዋሪዎቹ ይገልፃሉ።

 

ጉዳዩን በሽምግልና ለመጨረስ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙ የሀገር ሽማግሌዎችም ጭምር መታሰራቸውን የሚገልጹት፣ ተወካዮቹ ከታሰሩት ውስጥ ከንቲባ፣ ፖሊስ፣ የኢህአዴግ አባላት፣ የአስተዳደር ሠራተኞች፣ መምህራን፣ ተማሪዎችና ሌሎችም እንደሚገኙበት ጠቁመዋል።

 

”የፌደራል መንግሥት በጉዳዩ ጣልቃ ገብቶ፣ ያለ አግባብ የታሰሩ ወገኖቻችን እንዲፈቱ፣ እኛም መብታችን ተጠብቆ በሠላም እንድንኖር ያደርግልን፣ በስተርጅና ከምንኖርበት ቀዬ ተፈናቅለንና ሥራችንን በድለን አዲስ አበባ ላይ ላላስፈላጊ ወጪ ተደርገናል” ሲሉ አዲስ አበባ የሚገኙት ኮሚቴዎች ሲገልጹ፣ ቡታጅራ ከተማ የሚገኙት ደግሞ ”ወዳጅ ዘመዶቻችን መታሰራቸው ሳያንስ እኛም ከዛሬ ነገ እንታሰራለን በሚል የሰቀቀን ኑሮ እየኖርን ነው፣ የፌደራል መንግሥት ኃላፊዎች ለአንድ ሰዓት እንኳን መጥተው ለምን ችግራችንን አይፈቱልንም” ሲሉ ጠይቀዋል።

 

የደቡብ ክልል ፓሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ጀማል አብደላ፣ ዋና ኢንስፔክተር ሠለሞን ሙሉጌታና የደቡብ ከተማ ፖሊስ ዋና ኢንስፔክተር ከበደ ደበበ ለጋዜጠኞች መረጃ ሊሰጡ ቃል ከገቡ በኋላ፣ አሁን ባለው ሁኔታ መረጃ ቢሰጡ በቀጣዩ የምርመራ ሥራቸው ላይ እንቅፋት እንደሚፈጥርባቸው በመግለጽ ምርመራውን በጨረሱበት ወቅት ግን መረጃውን እንደሚሰጡ ተናግረዋል።

 

የደቡብ ክልል ፀጥታ አስተባባሪ ፓሊስ ዋና ኢንስፔክተር ብርሃኑ ቃለአብ ጉዳዩን በሚመለከት እንደገለጸው፤ በአሁን ሰዓት የቡታጅራና የመስቃን ወረዳ ፀጥታ በጥሩ ሁኔታና በሠላማዊ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝና ስለተፈጠረው ችግር በውል እንዳላወቀ፣ የተሰጣቸው ምክንያት ግን የንብረት መውደምና የአካል ጉዳት እንደተፈጠረና ኃይል በመያዝ ከደቡብ ክልል ወደ ቡታጅራ መምጣታቸውን ነው የተናገረው።

 

”በአጠቃላይ በቁጥጥር ስር ስለዋሉት ነውጠኞች የሚያውቁት በምርመራ ዘርፍ ያሉ ኃይሎች ምላሽ ይሰጣሉ፣ በሚታየው እንቅስቃሴ አሁን ሁሉም በቁጥጥር ስር ውለዋል ማለት ስለማይቻል ነቅቶ የመጠበቁ ኃላፊነቱ በኛ ላይ ብቻ ነው ያለው” ብሏል።

 

”ፀጥታውን ለማስፈን የተጠቀምነው ሕጉ በሚፈቅደው መጠን ነው” ያለው ኢንስፔክተር ብርሃኑ፤ “ከዚህ ጎን ለጎን ህዝቡን የማሳመን ሥራ እየሠራን ነው፣ ኅብረተሰቡም የራሱን ሃሳብ እየገለጸ ይገኛል” ቢልም፤ ከ50 በላይ የሚሆኑ የከተማው ነዋሪዎች በፍርሃትና በሰቀቀን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

 

በረብሻው መኻል በድንገት የቀኝ እጁን ያወጣው ተማሪ አብዱል ከሪም ”በአሁኑ ሰዓት በቡታጅራ ሆስፒታል ሕክምናዬን እየተከታተልኩ ነው” ሲል፣ የወረዳው ነዋሪዎች በበኩላቸው ደግሞ መብታችን ተከብሮ፣ በሠላም ወጥቶ የመግባት ኅልውናችን ሊጠበቅ ስላልቻለ ፌደራል መንግሥቱ አፋጣኝ መፍትሔ ይስጠን ይላሉ።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ