Journalist Meaza Birru & PM Dr. Abiy Ahmed

ጋዜጠኛ መአዛ ብሩና ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ

ኢዛ(ቅዳሜ መስከረም ፫ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. September 14, 2019):- ዛሬ መስከረም ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ለአንድ ሬድዮ ጣቢያ ጆሮውን ለመሥጠት መነጋገር ከጀመረ ቀናት አልፈዋል። ይህም በኢትዮጵያ ውስጥ አንድ በሥልጣን ላይ ያለ ጠቅላይ ሚንስትር ለግል ሚድያ ሰፊ ቃለምልልስ ለመሥጠት ተስማምቶ፤ ይህም እውን ኾኖ ዛሬ እንደሚተላልፍ ባለፉት ጥቂት ቀናት መነገሩ ነበር። በኢትዮጵያ የሚድያ ታሪክ እንደ መጀመሪያ የሚቆጠረውን ቃለምልልሱን ያደረገችው ደግሞ ጋዜጠኛ መአዛ ብሩ ናት።

ከጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ጋር ያደረገችውን ቃለመጠይቅ፤ ዛሬ ከዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ ብዙዎች ቀደም ብለው ተዘጋጅተው በጋራና በተናጠል በየቦታው ሲያደምጡ ቆይተዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች ወትሮ ቅዳሜና እሁድን ለእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ዓይንና ጆሯቸውን ቅድሚያ የሚሰጡ የእግር ኳስ አፍቃሪያን ሳይቀሩ የመአዛንና የጠቅላይ ሚንስትሩን የጨዋታ ቆይታ ሲያዳምጡም ነበር። የጠቅላይ ሚንስትሩ ቃለምልልስና የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታ በጋራ ሲደመጥና ሲታይ የነበሩባቸው ቦታዎች ነበሩ።

ዛሬ በሸገር የጨዋታ እንግዳ ኾነው የቀረቡት ጠቅላይ ሚንስትሩ አብይ አሕመድ ከመአዛ የተለያዩ ጥያቄዎች የቀረቡላቸው ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚንስትሩ ሠፋ ያለ ምላሽ ሰጥተውባቸዋል።

በዛሬው ቃለምልልስ ምላሽ ከሰጡባቸው ጉዳዮች ውስጥ በቅንጭብ ሲታይ፤

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ ስለኢትዮጵያ

”ኢትዮጵያን በጣም ከሚወዱ ዜጎችዋ አንዱ ነኝ። በጣም ነው አገሬን የምወደው።

”የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙርን ወይም ኢትዮጵያን የሚመለከት ጉዳይ ሲነሳ እንደማንኛውም ጊዜ በሙሉ ብቃት መቆም የምችል ሰው አይደለሁም።

”አገሬን በጣም አብዝቼ እወዳለሁ። ይቺ አገሬ እንደሚባልላት ተቀይራ ማየት በጣም በጣም እጓጓለሁ። እንደሚኾንም ደግሞ ልቤ በጣም ያምናል።

”አገሬን መውደድ በፍቅሯ ውስጥም ብልጽግናዋን መመኘት፣ በምኞት ውስጥም መትጋት፣ በትጋት ውስጥም ውጤት ማምጣት ነው የማስበው።

”የመጨረሻው ሕልሜ እንዲህ ታላቅ ብዬ የማምናት፣ ታላቅ ብዬ የምወዳት ከማንም የማላስተካክላት፣ ከማንም ልቃና በል የምትታየው የኔ አገር በማስባት ልክ ኾና ማየት ነው ምኞቴ።”

ጋዜጠኛ መአዛ ብሩ ከጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ጋር ያደረገችውንና የመጀመሪያውን ክፍል ቃለምልልስ ለማድመጥ እዚህ ይጫኑ!

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ