PM Dr. Abiy Ahmed

ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ

“የኛ ሐሳብ የማይስማማቸው ካሉ አማራጭ ያቅርቡ”

ኢዛ (ሰኞ ጥቅምት ፲፯ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. October 28, 2019)፦ ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ከመከካከያ ሚንስትሩ አቶ ለማ መገርሳና ከኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ጋር በመኾን ከአባገዳዎች፣ ከሃይማኖት አባቶችና ከተለያዩ የሕብረተሰብ ተወካዮች ጋር ተወያዩ።

በኦቢኤን በኩል ለተለያዩ መገናኛ ብዙኀን የተሠራጨው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በዚህ መድረክ ዋንኛ አጀንዳ በኦሮሚያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ውይይት የተካሔደው ጥቅምት 16 ቀን 2012 ዓ.ም. ነው።

እንደዘገባው፤ ተሳታፊዎቹ በወቅታዊ ጉዳዮችና የሕዝቡን አንድነት በማስመልከት ያሏቸውን ጥያቄዎችና ሐሳቦች በማንሳት ተወያይተዋል።

ከተሳታፊዎቹ ተነሱ ከተባሉት ሐሳቦች ውስጥ፤ ሐሰተኛ መረጃዎችን የሚያሠራጩ በእኛ ውስጥ ቦታ የላቸውም፣ ለአገሪቱ የሚቆረቆር ሰው ካለ ስለአገሪቱ ብቻ ይናገር ማለታቸውን ተደምጧል።

መንግሥትም የሕግ የበላይነትን ማስጠበቅ እንዳለበት ተሳታፊዎቹ መናገራቸውን የሚገልጸው ይኸው ዘገባ፤ ችግሮቻችንን ባለን ባህልና እሴት መሠረት በመፍታት አንድነታችንን ማጠናከር አለብን ስለማለታቸው ተጠቅሷል።

ሕዝቡን ማደናገር መቆም እንዳለበት፣ መገናኛ ብዙኀንም በሕግ አግባባ ሥራቸውን መሥራት እንዳለባቸው ተሳታፊዎቹ አመልክተዋል።

ረዥም መጓዝ ስለምንፈልግ፤ በአንድነት ኾናችሁ ሕዝቡን አስተባብሩ የሚልም ሐሳብ ከተሳታፊዎቹ ተሰንዝሯል።

ውይይቱን የመሩት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድም፤ “እኛ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄና ፌዴራል ሥርዓትን ወደኋላ ለመመለስ አንሠራም፤ ከእኛ የሚነሳ ሐሳብ የማይስማማው ካለ፤ ሌላ አማራጭ ሐሳብ ማቅረብ ነው” በማለት እንደተናገሩ ዘገባው ያሳያል።

“እርስ በርስ በመጎዳዳት መሻገር አይቻለም” ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ መንግሥት የፌዴራል ሥርዓቱን ወደኋላ የሚመልስ ምንም ዐይነት ሥራ እየሠራ ያለመኾኑን በመግለጽ ማብራሪያ ሠጥተዋል።

የአገር ሽማግሌዎቹና አባገዳዎቹ ያኮረፉ አካላትን እንዲያናግሩ፣ እንዲሁም መንግሥት ከሕዝቡ ሐሳብና ፍላጎት ውጭ ከወጣ ያኔ ውሳኔ አሳልፉ ሲሉ ስለመግለጻቸውም ዘገባው ያመለክታል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ