በነሜ/ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ላይ አዲስና ከባድ የሙስና ክስ ተመሠረተ
የቀድሞ የብረታ ብረትና ኢንጂንየሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው
የተከሰሱት ከ214 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ከተገዛና ጥራቱን ካልጠበቀ ራዳር በተያያዘ ነው
ኢዛ (ዓርብ ኅዳር ፲፱ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. November 28, 2019)፦ በነሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ላይ የፌዴራሉ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አዲስና ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸው ትናንት ፍርድ ቤት ቀርበዋል። ፍርድ ቤቱ ለዛሬ ጠበቃ ይዘው እንዲቀርቡ ቀጥሯቸዋል።
በቀድሞ የብረታ ብረትና ኢንጂንየሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘውና በሌሎች ሦስት ተከሳሾች ላይ ትናንት የተመሠረተባቸው አዲስ ክስ፤ ከራዳር ግዥ ጋር የተያያዘ ነው። ጥራቱን ያልጠበቀ ራዳር ከ214 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጪ በመግዛት በከባድ የሙስና ወንጀል በመጥርጠራቸው በአራቱም ግለሰቦች ላይ አዲስ ክስ ተመሥርቶ፤ ትናንት ፍርድ ቤት ቀርበው የክሱ ዝርዝር እንዲደርሳቸውና እንዲነበብላቸው ተደርጓል።
ከሜጀር ጄኔራሉ ክንፈ ጋር ከራዳር ግዥው ጋር በተያያዘ ክስ የተመሠረተባቸው ሦስቱ ተከሳሾች፤ ሌ/ኮሎኔል ፀጋዬ አንሙት፣ ኮሎኔል ሸጋው ሙሉጌታና ኮሎኔል መሐመድ ብርሃኑ መሆናቸውን ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አስታውቋል።
የፌዴራሉ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበው ክስ እንደሚያሳየው፤ ግለሰቦቹ የማይገባቸውን ጥቅም ለማግኘት በማሰብ በ2004 ዓ.ም. በኮርፖሬሽኑ የግዥ መመሪያ አንቀጽ 5.1 መሠረት፤ የግዢ ፍጻሜው አካል ግልጽነት፣ ተጠያቂነት፣ ጥራት ባለው በተቀላጠፈና ውጪ ቆጣቢ በኾነ መልኩ በተወዳዳሪ ዋጋ በጨረታ መፈጸም ሲገባቸው፤ መመሪያውን ወደጎን በመተው ያለጨረታ ግዥውን በመፈጸማቸው ነው።
የፌዴራል የአገር የመከላከያ ሚኒስቴር የግዥ ፍላጎት ሳይጠየቅ፤ ከሁለት የቻይና ኩባንያዎች ተመሳሳይነት ያላቸው ራዳሮች ግዥ መፈጸማቸውን የሚያስረዳ መኾኑን ይኸው የጠቃላይ ዓቃቤ ሕግ መረጃ ያስረዳል።
ስለከሱ ሌሎች ዝርዝር መረጃዎች የተጠቀሱ ሲሆን፣ እነሜጀር ጄኔራል ክንፈ በትናንትናው ዕለት በዋለው ችሎት ጠበቃ እንዲያቀርቡ ለፍርድ ቤቱ በመግለጻቸው፤ ፍርድ ቤቱ ለዛሬ ኅዳር 19 ቀን 2012 ዓ.ም. ጠበቆችን ለማቅረብ ቀነ ቀጠሮ ሠጥቷቸዋል። (ኢዛ)



