ኢትዮጵያ አንድ ልጅ አጣች
የአቶ ሹምዬ ተፈራ አባሜርጎ የቀብር ስነስርአት ተፈጸመ
"ክቡር ሊቀመንበር ምንም እንኳን እናንተ የአጼውና የካቢኔው ወንበር ቢሞቃችሁም እኛን ግን የፓርላማ ወንበር ለመውረስ የተወከልን ሳንሆን በአቧረ አቤታችን ተሰብስበን የሰራተኛውን ጉዳይ እንድንወያይ ቤታችን እንዲከፈትልን ነው ጥያቄያችን" አቶ ሹምዬ ተፈራ በደርግ መሪ ፊት የተናገሩት
Ethiopia Zare (ረቡዕ መስከረም ፯ (7) ቀን ፳፻፩ (2001) ዓ.ም. September 17, 2008)፦ የአቶ ሹምየ ተፈራ የቀብር ስነ ስርአት ዛሬ ሴፕቴምበር 17 ቀን 2008 ዓ.ም በቫንኮቨር-ካናዳ ተፈጸመ። በቀ.ኃ. ስላሴ ዘመን ማብቂያና በደርግ ዘመን መጀመሪያ የአቃቂ ጨርቃ ጨርቅና የሂልተን ሆቴል ሰራተኞች ማህበር መሪ በመሆን ያገለገሉና የሰራተኛውን መብት በማስከበር ከሚታወቁት ግርማቸው ለማና አበራ ገሙ ጋር በመሆን የሰሩ አንጋፋ ኢትዮጵያዊ መሆናቸው በቀብራቸው ስነስርአት ላይ ተወስቷል
አቶ ሹምዬ ተፈራ የአራት ልጆች አባት ሲሆኑ ከወጣትነት እድሜያቸው ጀምሮ ለሀገራቸው በሚያምኑበት አላማ በመትጋት ሲታገሉ የቆዩና በካናዳ የመጀመሪያ የሆነውን የቫንኮቨር ኢትዮጵያዊያኖች ኮሚኒቲ ካቋቋሙ ግለሰቦች አንዱ ሲሆኑ በማናቸውም ሰአት በማህበረሰቡ ስብሰባ በመገኘት የሚያስቡትን በድፍረት ሲናገሩ የቆዩ ነበሩ።በቀብሩ ስነስርአት ላይ በቫንኩቨር ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የህዝብ ብዛት መገኘቱ ታውቋል። በአቶ ሹምዬ ተፈራ አባሜርጎ የቀብር ስነስርአት ላይ የሲያትሉ ቅዱስ ገብርኤል አባት የሆኑትና በስደት የሚገኘው የኢትየጵያ ሲኖዶስ ጳጳሳት አቡነ ዮሐንስና አቡነ ሉቃስ ተገኝተው ጸሎተ ፍታት አድርገዋል። አቶ ሹምዬ ቫንኮቨር የምትገኘው ቅድስት ማሪያም ቤተክርስቲያን መስራች ነበሩ።
ለአቶ ሹምዬ ባለቤት አወ/ሮ እጅጋየሁና ልጆቻቸው እንዲሁም ለመላ ቤተሰብና ጓደኞቻቸው መጽናናትን እንመኛለን::
በማተቡ፡ በእምነቱ ጸንቶ፤ ስለእምነቱ ኖሮ በእምነቱ ያለፈ አንጋፋ ኢትዮጵያዊ
የአቶ ሹምዬ ተፈራ አባሚርጎ የሕይወት ታሪክ
“በማተቡ!!” አላቸው ለሀያ ዓመት አካባቢ የሚያውቃቸው አቶ ጥጋቤ ሽጉጥ። “ከዚያ ሁሉ እሳት ውስጥ ይወጣል ብሎ የገመተ የለም” አሉ፡ ታናሽ እህታቸው ወ/ሮ አስናቀች ተፈራ እና የረጅም ግዜ የትግል አጋራቸው አቶ ወልዴ ቱቶ። “እኔ ምንም የምናገርበት አንደበት የለኝም። በህይወቴ፡ ከሱ ጋር ከተገናኘሁ ጀምሮ “የማስመሰል” ሳይሆን፡ እውነተኛ ከፍተኛ አክብሮትና ፍቅር እንዳለኝና እንዳገኘሁ ብቻ እንጂ !! ከተገናኘንበት ግዜ ጀምሮ ጸባዩ አንደበቱ ቋንቋው ሳይቀየርብኝ፡ እንዳገኘሁት የተለየሁት፡ የህይወት አጋሬ፡ ትዳሬ፡ ጋሻዬ ነው።” “በትዳር ዘመናችን አንድም ቀን ሽምግልና ገብቶብን የማያውቀውን፡ እኔ ብዬ ወይም ጠይቄ አንድም ቀን ከልክሎች፡ እንቢኝ ብሎ የማያውቀውን ባሌን ነው ያጣሁት” አሉ ባለቤታቸው ወ/ሮ ጂጂ ይገዙ።
ይሄ ብቻ አይደለም፤ ዝርዝሩ ይቀጥላል። “በቀይ ሽብር ሰው በተገደለ ቁጥር፡ እሱ ነው እያልኩ፡ ሬሳ ስቆጥር እውል ነበር። የቀበሌ አመራሮች ነጻ እርምጃ እንዲወስዱ ስልጣን በተሰጣቸው ሰዓት፡ ከዚያ ተርፎ ይወጣል ብዬ አልገመትኩም። ከዚህ ሞት ተርፎ “ሌላ ቦታ ሞተ” ብባል ግን አላለቅስም ብዬ ቃል ገባሁ።” ያሉን፡ ለስድስት ዓመታት ሞቷል ብለው እርማቸውን አውጥተው፡ ጥቁር ለብሰው የኖሩት፤ ከሀያ ዘጠኝ ዓመት መለያያት በኋላ ያገኟቸው ታናሽ እህታቸው ወ/ሮ አስናቀች ናቸው።
ይሄ ባለፈው ቅዳሜ ባስደንጋጭ መልኩ የተቋጨው የወንድማችን፡ የአባታችን፡ የአጋራችን የአቶ ሹምዬ ተፈራ የሕይወት ጉዞ የዛሬ ስልሳ ስድስት ዓመት ነበር የጀመረው። መስከረም፡ የከተራ እለት። ትውልዳቸውና፡ የልጅነት ሕይወታቸው፡አቶ ሹምዬ ተፈራ፡ ከአባታቸው፡ ከአቶ ተፈራ አባሚርጎ፡ ከእናታቸው ወ/ሮ ጌጤ ቱሉ፡ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር፡ መስከረም 16 ቀን፡ ሺህ 9 መቶ 35 ዓ.ም.፤ በሸዋ ክ/ሀገር፡ ከአዲስ አበባ ወጣ ብላ በምትገኘው፡ “ሙሎ” ከተማ ከጭቁን ቤተሰብ ተወለዱ።
አባታቸው በልጅነታቸው በሞት ስለተለይዋቸው፡ እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ፡ እናታቸው ወደአዲስ አበባ አምጥተዋቸው፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን፡ በአርበኞች አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሩ። የሁተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በመድሀኔዓለም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠናቀቁና በመጀመሪያ ያኔ ኢንዶ ቴክስታይል፡ አሁን አቃቂ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ውስጥ ተቀጠሩ።
እዚያ ነው የአቶ ሹምዬ ተጋድሎ የሚጀምረው። እኚያ ከኛ ጋር እንደ ተራ ሰው ሲመላለሱ የነበሩት አቶ ሹምዬ፡ በሂልተን ሆቴልም ይሁን በኢንዶ ጨርቃጨርቅ፤ በተለይ ለሰራተኛው የዋሉትን ውለታ ሲጠቅሱ፡ የስራ ባልደረቦቻቸው ሲቃ እያነቃቸው ነበርና፤ አምስት ስድስት ግዜ ውይይታችንን ማቋረጥ ነበረብን። በአቃቂ ጨርቃጨርቅ ካከናወኗቸው ተግባራት ውስጥ፡ በረጅም ግዜ የትግል አጋራቸው አነጋገር የሚከተሉት ይገኙበታል።
በ1960ዎቹ መጀመሪያዎቹ ላይ፡ በአቃቂ ኢንዶ ቴክስታይል ፋብሪካ ውስጥ በነበረውን አሰቃቂ የስራ ሁኔታ፡ ሰራተኛው ምንም አይነት መፈናፈኛ በሌለበት፡ በጥጥ ብናኝ ሳምባው እየተሞላ በሚሰቃይበት ጊዜ፡ “ያ መወገድ አለበት አሰሪዎች ለሰራተኛውም የተሻለ የስራ ሁኔታ ሊፈጥሩ ይገባል” በሚል ጽኑ እምነት፡ ህይወቱን ለኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበር ለመስጠት ወስነው የተነሱ፡ የጊዜው ወጣት የኢትዮጵያ ሰራተኞች መሪ ነበሩ። በዚህም ጽኑ እምነታቸው፡ የተነሳ ለ3 አመት የኢንዶ ቴክስታይል ሰራተኞች የስራ ሁኔታ (working condition) እንዲሻሻል ብዙ መስዋእትነትን የከፈሉ ሰውና በዚህም ቆራጥ አይታክቴ ትግላቸው፡ የሰራተኛው መብት እንዲሻሻል የተሻሉ የህብረት ስምምነቶችን ያስገኙ፡ ለዲሞክራሲና ለፍትህ የበላይነት የቆሙና በጽናት የታገሉ፡ በጽናት መሞትን የህይወታቸውና የትግል ዝማሬያቸው ያደረጉ ኢትዮጵያዊ ነበሩ። ያኔ በአቃቂ በሰቃ፡ ትርፋቸው ብቻ የሚያንገበግባቸው የህንድ ባለሀብቶች ስስት ምክንያት የተነሳ፡ በተለይ ሴቶች ሰራተኞች በጥቂት ወጪ መከላከል ይቻል በነበረ የኢንዱስትሪ ብናኝ፡ በየቀኑ በሳንባ ነቀርሳ ሲረግፉ፡ “ይሄንንስ ቆሜ አላይም ብለው፡” ያንን በማስቀየር የሰራተኛው መብት እንዲጠበቅ አድርገዋል።
በወቅቱ ከህንድ የፋብሪካው ባለሀብቶች ጉቦ የሚበሉ የንጉሱ ሚኒስትሮችና ባለሟሎች የሰራተኛው መብት እንዳይጠበቅ ብዙ ተጽእኖና ማስፈራሪያ ቢያደርጉባቸውም፡ አቶ ሹምዬ ግን እስከመጨረሻው ያንን ተቋቁመው ለውጥን አምጥተዋል።ይሁን እንጂ፡ ይላሉ ጓደኛቸው፡ “አቶ ሹምዬ ተፈራ በነበረው ቆራጥና ቅን የሰራተኛው መብት ተከራካሪነቱ የተነሳ፡ እስከጠቅላይ ሚኒስትሩ በደረሰ ከአሰሪዎችና የመንግስት ተወካዮች ጋር በየተደረገ የክስ ሂደት በተላለፈ ትእዛዝ፡ የኢንዶ ቴክስታይል(አቃቂ ጨርቃጨርቅ) ስራውን እንዲያጣ ተደረገ።” የአቶ ሹምዬ ተልእኮ ግን አላበቃም ነበርና፡ ከአቃቂ ጨርቃጨርቅ በመንግስትና በአሰሪዎች ትእዛዝ ከስራቸው ሲባረሩ በአዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል በሂሳብ ሰራተኝነት ተቀጠሩ።
እሳቸው፡ የሰራተኛው ቦርድ አባል ሆነው እንዲሰሩ ተመርጠው ሲያገለግሉ፡ በሰራተኛና በአሰሪ መካከል ባለው ውጥረት አለማቀፋዊ ልምድ ያለው የሂልተን ተወካይ ተጠርቶ፡ ይህ አለማቀፋዊ ልምድ አለው የተባለው የአሰሪዎች ተወካይ 23 የቦርድ አባላትን ሰብስቦ “ስኮላር ሺፕ፡ ሹመት፡ የደመወዝ እድገት አግኝታችሁ ብትኖሩ ይሻላችኋል” ብሎ ማባበያ አቀረበ። ከ23ቱ የቦርድ አባላት 3ቱ ብቻ ሲቀሩ፡ የተቀሩት የሰራተኞችን ማህበር፡ አፍርሰው ሄዱ። በወገኖቹ ላይ መደራደር የማይዋጥለት አቶ ሹምዬ ግን፡ እነዚህን 3 ግለሰቦች ይዞ በውድቅት ጨለማ ሰራተኛውን በንግድ ስራ ት/ቤት አዳራሽ ሰብስቦ፡ በሊቀመንበርነት ከተመረጠ በኋላ፡ የቦርድ አባላቱን አሟልቶ የሰራተኛው መብት እንዲከበር ያደረገ ቆራጥና ጀግና ታጋይ ነበር።
በዚህም የተነሳ ሲገባ ሲወጣ፡ በቀን ከ3-5 ጊዜ እንዲፈርምና ተስፋ ቆርጦም ስራውን እንዲያቆም ጥረት ቢደረግም፡ በነበረው ጽኑ እምነትና ቆራጥ አላማ ስራውን ቀጥሎ፡ በሰራተኞችና በአሰሪዎች መካከል የጋራ ስምምነት እንዲፈረም ያደረገ በጽናት ትግል የሚያምን ሰው ነበር።የአቶ ሹምዬ ታሪክ እንዲህ አጭር አይደለም። አቶ ሹምዬ በሂልተን ሆቴል የሂሳብ ሹም ሆነው ተቀጥረው ሲሰሩ በነበረበት ጊዜ፡ የሰራተኛው ተወካይ ሆነው ሲያገለግሉ፤ በአዲስ አበባ ሂልተን ሰራተኞችና በአለማቀፍ የሂልተን ሰራተኞች መካከል በነበረ እኩልነት የሌለበት አሰራር፡ የኢትዮጵያ ሂልተን ሰራተኞች የአገልግሎት ክፍያ ሳይከፈላቸው፡ በአለማቀፍ የሂልተን ሰራተኞች ግን ቋሚ ህግ ሆኖ ይከፈላቸው እንደነበር በማረጋገጥ፡ የኢትዮጵያ ሂልተን ሰራተኞችም የዚህ አለማቀፍ የሰራተኞች መብት ተጠቃሚ መሆን አለባቸው በማለት ተከራክረዋል።
በወቅቱ ያገኙት መልስ “የኢትዮጵያ ሆቴሎች በሙሉ ካልተስማሙበት ሂልተን ለብቻው የሚፈጥረው ህግ የለም” ቢባልም፡ አቶ ሹምዬ አሁንም ይህንን ታግሎ ማግኘት እንዳለበት በማመን የኢትዮጵያ ሆቴሎችን አመራር እየሰበሰበ፡ ይህንን መሰረታዊ የሆነ የሰራተኞች ጥቅም ማስከበር እንዳለባቸው ሲያግባባና ሲያወያይ ለብዙ ጊዜ ከጣረ በሗላ፡ በመጨረሻ የሁሉንም ፊርማና ስምምነት በማግኘት ለኢትዮጵያ ሆቴሎች ሰራተኞች የአገልግሎት ክፍያ ህግ ሆኖ ጸድቆ በኢትዮጵያ እንዲሰራ ያደረገ አንጋፋ የሰራተኞች መሪ ነበሩ።
ምን ይሄ ብቻ፡ በሆቴሎች አካባቢ እንደ አልባሌና ከሰው በታች ይታይ የነበረው ሰራተኛ፡ በእኩልነትና በሰውነት እንደሰው እንዲታይ ከማድረጋቸውም ባሻገር፤ የቀን ውሎ 0.75 ሳንቲም ሆኖ ሰራተኛው ይበዘበዝና ይታሽ በነበረበት ሰዓት፡ ወደ ሶስት ብር እንዲያድግ የታገሉ ጭቁን ነበሩ።አቶ ሹምዬ ተፈራ የሰራተኛው ማህበር ተወካይ ሆኖ በእስራኤል ሀገር ለ7ወር በትምህርት ላይ ቆይቶ ተመልሷል። ከተመለሰ በኋላም፡ የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበር የህግ አማካሪ ከነበረው ከአቶ ግርማቸው ለማ ጋር ምክትል ሆኖ፡ እንዲሁም፡ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበር አመራር ከነበሩት ከእነ አቶ አበራ ገሙ ጋር የሰራና፡ በሐረር፣ በሸዋና በጅማ ጠቅላይ ግዛቶች በመዘዋወር ሰራተኞችን በማህበር በማደራጀት ያገለገለ ኢትዮጵያን አብጥርጥሮ የሚያውቅ፡ ተተኪ የሌለው አደራጅና ታጋይ መሪ ነበር።አቶ ሹምዬ ተፈራ ቆራጥ ደፋርና ሀሳቡን በልበ ሙሉነት የሚናገርና ለቆመለት አላማ ህይወቱን ለመሰዋት ቅንጣት ታክል እንኳ ቅር የማይለው ሰው እንደሆነ የተጓዘባቸው የትግል ታሪኮች ህያው ምስክር ናቸው።
ደርግ የሰራተኛውን የሙያ ማህበር ኢ.ሰ.አ.ማ.ን በአዋጅ ዘግቶ በምትኩ የራሱን ተለጣፊ የሙያ ማህበር ለማቋቋም ሲል በሊቀመንበሩ መንግስቱ ኃይለማሪያም ትእዛዝ፡ 120ዎቹ የደርግ ተወካዮች በተገኙበትና በብሄራዊ ሸንጎ አዳራሽ በተጠራው የሰራተኛው ማህበር ተወካዬች ስብሰባ ላይ፡ ሊቀመንበሩ ስብሰባውን ለውይይት ከፍተው አይናቸውን እያጉረጠረጡ ችግራቸውን እንዲያስረዱ ሲጠይቁ፤ አዳራሹ በዝምታ ተውጦ፡ በፍርሀት ተሸብቦ በነበረበት ሰአት፡ ደፋሩ ሹምዬ ተፈራ ግን፡
“ክቡር ሊቀመንበር ምንም እንኳን እናንተ የአጼውና የካቢኔው ወንበር ቢሞቃችሁም፡ እኛ ግን የፓርላማ ወንበር ለመውረስ የተወከልን ሳንሆን በአቧራ ቤታችን ተሰብስበን የሰራተኛውን ጉዳይ እንድንወያይ ቤታችን እንዲከፈትልን ነው ጥያቄያችን።” ሲል በድፍረት የአምባገነኖቹን ቁንጮ የተጋፈጠ ሰው ነበር።
በዚያ ድፍረታቸውም ልክ እንደ ንጉሱ ዘመን፡ በደርግም ጥርስ ውስጥ ገቡ። በ1967/68 ዓ.ም. የደርግ ባለስልጣናት ሊረሽኗቸው ካሰለፏቸውና ሰራተኛው እኛንም አብራችሁ ጨርሱን እንጂ አናስገድልም ብሎ በተአምር ካተረፋቸው 54 የሰራተኛ መሪዎች ውስጥ አንዱ ነበር። ያንን ሁሉ ተመልክተው ነው፡ እህታቸው ወ/ሮ አስናቀችና የትግል አጋራቸው አቶ ወልዴ ቱቶ “ከዚያ እሳት ውስጠ ይወጣል ብሎ የገመተ የለም ያሉት።” አቶ ሹምዬ ከዚያ ሁሉ እሳት ውስጥ ቢተርፉም፡ ትግላቸው ግን ወደ ሌላ ደረጃ አደገ እንጂ ወደኋላ አላፈገፈጉም።
በበረሀ፡ በሜዳው፡ በአሲምባ
የሰራተኛው ተወካይ በነበሩበት ግዜ ሁሉ፡ አብረዋቸው የነበሩት የትግልና የስራ ባልደረቦቻቸው እንደሚመሰክሩት፡ ሌሎች ለመናገር የፈሩትንና ያፈሩትን በልበ ሙሉነትና በድፍረት አደባባይ ወጥተው ሲናገሩ፡ የዘመኑ የፖለቲካ ባህል ነበርና፡ ይሄ ድፍረታቸው በንጉሱም ይሁን ከንጉሱ በቀጠለው ወታደራዊ አገዛዝ ዘንድ አልተወደደላቸውም። ጥርስ ውስጥ አስገባቸው።
ስለዚህም ከ1975 ዓ.ም. ጀምሮ ለመገደል ሲፈለጉ፡ ለሁለት ዓመት ሕቡእ ገቡ። በህቡእ በቆዩበት ሰዓትም፡ ለሞት የሚፈለጉትን በማትረፍና ወደውጭ በማስወጣት ሲያስተባብሩ ቆይተው፡ በእስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ አልፈዋል። ግድያው እየከፋ ሲመጣም ነው፡ የትጥቅ ትግል ለማድረግ በ1976 መጨረሻ፤ ወደ አሲምባ፡ በረሀ ወረዱ። አቶ ሹምዬ፡ ሁልግዜም ቆሞ ከመሞት፡ እየታገሉ መሞትን ስለሚመርጡ ነው ወደ አሲምባም የገቡት። ለህዝብ እንጂ።
እህታቸው ወ/ሮ አስናቀች፡ በዚህ የቀብር ስነ-ስርአት ላይ የተገኙ ጓዶቻቸውም እንደሚመሰክሩት፡ ከልጅነታቸው ጀምሮ የሕዝብ ጉዳይ የሚያንገበግባቸው፡ ለሰራተኛው መብት በመታገል የልጅነት እድሜያቸውን የገፉ ሰው ነበሩ። ሰላማዊ ሰልፍ በተከለከለ ጊዜ እንኩዋን፡ ሰው እንቀብራለን ተብሎ የሀሰት የአስከሬን ሳጥን ተሸክመው፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ስብሰባን ሊያስተናግዱ ሽር ጉድ ይሉ የነበሩትን ንጉስ በማሳጣትና የሰራተኛው የመደራጀት መብት እንዲፈቀድ የታገሉና ያስታገሉ ሰው ናቸው። በሜዳ ከሳቸው ጋር የነበሩት፡ ሌላ ወዳጃቸው የሜዳ ውሏቸውን እንዲህ ብለው ተርከውልናል።
በ1976/77ወደ አሲምባ ገብተው፡ በሰራዊቱ የማሰልጠኛ ክፍል ውስጥ የሚሰጠውን ስልጠና ወስደው፡ በተለያየ እርከን በሀላፊነት ሲያገለግሉ ቆይተው፡ በ1978/79 ዓ.ም. በሰራዊቱ ላይ በሕዝባዊ ወያኔ አርነት ትግራይ/አሁን ወያኔ በምንለው በደረሰበት ጥቃት ምክንያት፡ ሰራዊቱ ቦታ ለቅቆ ወደ ቤጌምድር ሲሻገር እሳቸውም ትግሉን ለመቀጠል ወደዚያው አብረው አምርተዋል።
በዚያ ሂደት ውስጥም፡ አቶ ሹምዬ ከራሳቸው አስቀድመው፡ ሌሎች የሰራዊቱ አባላት በሰላም እንዲያልፉ በማድረግ፡ የሰራዊቱን የገጠር ትግል በማስተባበር፤ የማእከላዊ ትጥቅና ስንቅ አቅርቦትን በማደራጀት ሲያገለግሉ ቆይተዋል። እኚሁ የትግል አጋራቸው እንደሚመሰክሩትም፡ በሰራዊቱ ውስጥ በተለያዩ ወቅቶች የሚነሱትን ችግሮች በሰላም እንዲፈቱ፡ ያላሳለሰ ጥረት ያደረጉ ታላቅ የድርጅታቸውም የአገራቸውም ሰው ነበሩ። መስዋእትነት እስከመክፈል ድረስ ተዘጋጅተው በታላቅ ትጋትና አንክሮ ለትግሉ አስተዋጽኦ ሲያደርጉ የነበሩ ታጋይ ናቸው።
ሰራዊቱ ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት ሲደርስበት ለሌሎች የመዳንን ቅድሚያ ሲሰጡ ቆይተው፡ ሰራዊቱ በ1982 ወደ ሱዳን ተሰዶ በገባ ግዜ፡ እሳቸውም ከስድስት ዓመት ትግል በኋላ ወደ ሱዳን ተሰደዱ። በሱዳንም፡ ከድርጅታቸውና ከሌሎች የሰራዊቱ አባላት ጋር ለትግሉ አስተዋጽኦ ሲያደርጉ፡ እንዲሁም በስራ በመሰማራት ኑሮዋቸውን ሲረዱ ቀይተው፡ በ1983/84 ዓ.ም. ወደ ቫንኩቨር/ካናዳ መጡ።
ደግሞ ወዲህ ወደካናዳ፡ ወደምእራቡምናልባት፡ በቅርብ ግዜ ለመጣን ሰዎች ካልሆነ በስተቀር፡ አቶ ሹምዬ ላለፉት 25 ዓመታት፡ በቫንኩቨር፡ በካናዳ እና በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ውስጥ ሲያበረክቱ የኖሩትን አስተዋጽኦ መዘርዘር ለቀባሪው ማርዳት ይሆንብናል። ይሁን እንጂ፡ ለታሪክ ተመዝግቦ እንዲቀርና፡ እንዳይረሳም ጭምር፡ ጥቂቱን ልናወሳ እንሻለን። በቫንኩቨር ውስጥ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ለመጀመሪያ ግዜ እንዲቋቋም በማድረግ፡ ማህበረሰቡ ከመንግስት ፈንድ እንዲያገኝና ቢሮ አቋቁሞ ሶስት ሰራተኞች ቀጥሮ እንዲያንቀሳቅስ በማድረግ የሰሩ የማህበረሰቡ መስራችና መሪ ናቸው።
ከዚያ ግዜ ጀምሮ፡ በሞት እስከተለዩባት እለት ድረስ በህመማቸው ወቅት እንኳን ከማህበረሰቡ አልተለዩም። የኢትዮጵያ ስም በተጠራበት ቦታ ሁሉ ጋሽ ሹምዬ አሉ። አሁን በስልጣን ላይ ባለው ስርአት ንጹሀን ወጣቶች በተለያየ ሰዓት ሲገደሉ፡ ተቃውሞን ለመግለጽ በሚጠሩ ሰላማዊ ሰልፎች ላይ ሁሉ ግንባር ቀደም ሆነው፡ ያለኩራትና ትእቢት፡ ይልቅስ በትህትናና በቁጭት፡ መፈክር በማንገብ፡ መፈክርም በማሰማት፡ ከሮብሰን፡ አደባባይ እስከ አሜሪካን ኤምባሲ፡ ከቫንኩቨር ሰን እስከ ሲቢሲ የተሰለፉ፡ የማይደክማቸው፡ የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ ሁሌም የሚያስጨንቃቸው፡ የሚያንገበግባቸው ታላቅ ኢትዮጵያዊ ናቸው።
እስከ እለተ ሞታቸው ድረስ፡ የኢትዮጵያ ፍቅር እያቃጠላቸው፡ ህመማቸው እንኳን ሳይገታቸው በኢትዮጵያዊያን መድረክ ላይ መገኘታቸውን መስክረናል። ባለፈው የፈረንጆቹ ነሀሴ ወር፡ በኢትዮጵያ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች በተዘጋጀ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ምሽት ላይ፡ ብዙዎች በሚያሳምንም በማያሳምንም ምክንያት ሳይገኙ ሲቀሩ፡ እሳቸው ግን እዚያ ነበሩ። ባመኑበት ዓላማ፡ እስከመጨረሻው ድርጅታቸውንም፡ አገራቸውንም እንዳገለገሉ፡ ለራሳቸው፡ ለህዝባቸው፡ ለአገራቸው እና ለድርጅታቸው እንደታመኑ፡ እስከመጨረሻውም በእምነታቸው ጸንተው፡ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት፡ በተወለዱ በስልሳ ስድስት ዓመታቸው፡ ከአገራቸው በወጡ ደግሞ በ33 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
አቶ ሹምዬ የአራት ልጆች፡ ማለትም የያሬድ የሲራክ የዮዲት እና የቅዱስ አባት ከመሆናቸውም ባሻገር፡ ቤተሰባቸውን አጥብቀው እንደሚወዱ የረጅም ግዜ ባለቤታቸው ወ/ሮ ጂጂና ሌሎች ወዳጆቻቸው ይመሰክራሉ።
እንደ ማሳረጊያ፡ እንደ አስተያየት
የሕይወት ክፋቷ፡ የሰው ልጅ ገድሉ፡ የሰው ልጅ መልካም ስራው፡ የሰው ልጅም ለሰው ልጅ ያደረገው ሰናይ ምግባር ጎልቶ የሚወጣው፡ ከዚህ ዓለም በሞት ሲያልፍ ነው።
አቶ ሹምዬ በመካከላችን፡ እንደተራ ሰው ሲመላለሱ፡ እንደ እኩያና እንደ አዋቂ ስንከራከራቸው፡ ስንነተርካቸው፡ አንድም ቀን ግን ከጭቁን ቤተሰብ ተወልደው፡ ከልጅነታቸው አንስቶ ለዚህ ጭቁን ህዝብ ሲታገሉ መቆየታቸውን፡ ከአቃቂ በሰቃ እስከ ሂልተን ሆቴል፡ ከአሲምባ እስከ ቤጌምድር፡ ለኢትዮጵያዊያን ነጻነትና መብት መታገላቸው ያልተገለጠልን ብዙዎች እንኖራለን። አቶ ሹምዬ ተፈራ ኦሮምኛ፡ አማርኛ እንግሊዘኛ አቀላጥፈው የሚናገሩ፡ የኢትዮጵያን ክፍለ ሀገራት፡ ከሰሜን እስከ ደቡብ አሳምረው የሚያውቁ፡ አቶ ጥጋቤ እንደገለጣቸውም፡ “በማተቡ፡ ከእምነቱ ፈቀቅ ሳይል የሞቱ ንጽህ ኢትዮጵያዊ” ናቸው።
የአቶ ሹምዬ ሞት በማህበረሰባችን ውስጥ የሚያመጣውን ክፍተት እና ጉዳት ለመረዳት፡ ብዙ መቆየት አያስፈልገንም። ከእንግዲህ የሚቀልደው፡ ሰልፍ የሚሰለፈው፡ መፈክር የሚያሰማው፡ ስለኢትዮጵያዊያን ጭቁኖች የሚሟገተው፡ ለልጆቹ ሟች ሹምዬ በመካከላችን የለም። ስራውና ታሪኩ ግን ዘወትር ከኛ ጋር ይኖራል። ፈጣሪ ነፍሱን በገነት ያኖራት ዘንድ እንማጸናለን።
ለአቶ ሹምዬ ቤተሰቦችና ወዳጆቻቸውም መጽናናትን አጥብቀን እንመኛለን።
መስከረም 17 ቀን 2ሺህ 1 ዓ.ም.፣ ቫንኩቨር፣ ካናዳ



