የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በጋራ መግለጫ ሠጡ

ኢዛ (ኀሙስ ጥር ፳፩ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. January 30, 2020)፦ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የታገቱት የደንቢ ዶሎ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ያሉበትን ቦታ በተመለከተ ፖሊስ መረጃ እንዳለው ገልጸዋል። ይህ የተገለጸው ትናንት ጥር 20 ቀን ማምሻውን ሦስት የመንግሥት ተቋማት በጋራ በሠጡት መግለጫ ነው።

ኮሚሽነር እንዳሻው ጣሰው በጉዳዩ ላይ ክትትል እየተደረገ እንዳለ ጠቁመው፤ ጉዳት ደርሶባቸዋል ስለተባለው ግን ፖሊስ ምንም ዐይነት መረጃ እንደሌለው አሳውቀዋል። በአካባቢው ለጥንቃቄ ሲባል ስልክንና ኢንተርኔት መቋረጡንም ጨምረው ገልጸዋል።

መግለጫውን የሠጡት እንደሻው ጣሰው የፊደራል ፖሊስ ኮሚሽነር፣ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዲኤታና አቶ ንጉሱ ጥላሁን በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት የፕሬስ ሰክሬታሪያት ኃላፊ ናቸው።

ሦስቱ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ይህንን መግለጫ ለመሥጠት የተገደዱት ባለፈው ማክሰኞ ጥር 19 ቀን በሃያ ዘጠኝ የአማራ ክልሎች “እኅቶቻችን ይፈቱ!” በሚል መሪ መፈክር ስር ከፍተኛ የተቃውሞ ሰልፍ መካሔዱን ተከትሎ በዕለቱ የአማራ ክልል ብሔራዊ መንግሥትም “የሕግ የበላይነትን በማጠናከር የዜጎችን ደኅንነት እናስጠብቃለን!” በሚል ላወጣው መግለጫ መልስ ለመሥጠት እንደኾነ ይታመናል።

የመግለጫው ዐብይ ቃል ተማሪዎቹ አንፋሎ ወረዳ ሱዲ በሚባል ቀበሌ ኅዳር 25 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደተያዙ የሚያመለክት ሲሆን፣ መታገታቸውም ለፖሊስ ሪፖርት እንደተደረገ መከላከያ ሠራዊት ወደሥፍራው ገብቶ 21 ተማሪዎችንና ተጨማሪ ሰዎችን ማስለቀቁን አሳውቀዋል።

አሁን በሕዝብና በወላጆች ማብራሪሪያ እንዲሠጥ የተጠየቀበት የ17 ተማሪዎች ጉዳይም አንስተው ሲያብራሩ፤ ከ17 ውስጥ 12ቱ የደንቢዶሎ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ሲሆኑ፤ አምስቱ ግን የዩኒቨርሰቲው ተማሪዎች እንዳልኾኑ ገልጸዋል። በዚሁ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ዘገባ በሳምንቱ አንኳር ወሬዎች አምዳችን ይዘን እንቀርባለን። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ