በ22ቱ ግጭት ሕይወታቸው ያለፉ ወጣቶች የቀብር ሥነሥርዓት ተፈጸመ
በ22 ለተገደሉት ወጣቶች (ሚሊዮን ድንበሩና ሚካኤል ፋኖስ) በሺህዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በተገኙበት ፀሎተ ፍትሃት በቦሌ መድሃኒዓለም ሲካሔድ፤ (ሐሙስ ጥር 28 ቀን 2012 ዓ.ም.)
ዛሬ የሦስተኛው ወጣት ሕይወት አልፏል
ኢዛ (ሐሙስ ጥር ፳፰ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. February 6, 2020)፦ ለትናንት አጥቢያ ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት በኋላ፤ በአዲስ አበባ በ22 አካባቢ ከቤተክርስቲያን ግንባታ ጋር ተያይዞ ተፈጠረ በተባለ ግጭት ሕይወታቸው ያለፈ የሁለት ወጣቶች ሥርዓተ ቀብር ዛሬ ጥር 28 ቀን 2012 ዓ.ም. በሺህዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በተገኙበት ተፈጸመ። ሦስተኛውና የ17 ዓመቱ ወጣት ሕይወት ማለፉም ታውቋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀጳጳስ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ የተመራ ፀሎተ ፍትሃት በቦሌ መድሃኒዓለም ከተደረገ በኋላ፤ የቀብር ሥርዓታቸው በገርጂ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል።
አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት ባሉበት ባንዲራ የታጀበው የሁለቱ ወጣቶች ሥርዓተ ቀብር፤ መንግሥት ወንጀለኞችን ለፍርድ ያቀርብ ዘንድ የተጠየቀበትም ነበር።

ከአንድ ቀን ቀደም ብሎ በ22 አካባቢ ቤተክርስቲያን ለመገንባት ተንቀሳቅሰዋል በተባሉና በጸጥታ ኃይሎች መካከል ተፈጠረ በተባለው ግጭት፤ አቶ ሚሊዮን ድንበሩና አቶ ሚካኤል ፋኖስ የተባሉ ወጣቶች ሕይወታቸው አልፏል። በውድቅት ሌሊት በተፈጸመው ድርጊት፤ የሰው ሕይወት ያጠፉትና የድርጊቱ ፈጻሚዎች እስካሁን አልተለዩም።
ከዚሁ ድርጊት ጋር ተያይዞ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂንየር ታከለ ኡማ፤ የሟች ቤተዘመዶች ጋር በመሔድ ጭምር ያጽናኑ ሲሆን፣ ከዚያ በኋላ በሠጡት መግለጫ የሰዎች ሕይወት እንዲጠፋ ምክንያት የኾኑ አካላት ተጠያቂ ይኾናሉ ብለዋል።
እስከትናንት ማምሻ ድረስ በዚሁ ጉዳይ የተጠረጠሩ 7 ሰዎች መታሰራቸው የተገለጸ ሲሆን፣ አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያመለክቱትም በድርጊቱ ዙሪያ አሁንም የተለያዩ አስተያየቶች እየተሠጡ ሲሆን፣ አስተዳደሩ ድርጊቱ ከውቅናው ውጪ መኾኑን አሳውቋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያም በዚህ ድርጊት የተሳተፉ አካላት ለሕግ ይቀርቡ ዘንድ የጠየቀች ሲሆን፣ በጉዳዩ ላይ የሚደረስበት መረጃ መንግሥት ለሕዝብ ይፋ እንዲደረግም ጠይቃለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ለትናንት አጥቢያ ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት በኋላ በተፈጸመው በዚሁ አሳዛኝ ድርጊት ከቆሰሉና ሕክምና ሲደረግላቸው ከነበሩት መሐል አንዱና አሥራ ሰባት ዓመቱ እንደኾነ የተነገረው አንድ ወጣት ዛሬ ሕይወቱ ማለፉ ታውቋል።
በትናንትናውና በዛሬው ዕለት የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በከፍተኛ ኀዘን ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ዛሬ ዘጋቢ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች፤ “ከተማዋ ከባድ የኀዘን ድባብ አጥልቶባታል”፣ “መንግሥት የሚያስተዳድራት አትመስልም”፣ “እውነት መንግሥት አለ ወይ?”፣ … በማለት አስተያየት ሠጥተዋል። ያነጋገርናቸው እነዚሁ ነዋሪዎች፤ መንግሥት ተጠያቂዎችን ሕግ ፊት አቁሞ ለሕዝብ ማሳየት ይገባዋል ብለዋል። (ኢዛ)
የወጣቶቹ ሚሊዮን ድንበሩና ሚካኤል ፋኖስ ሥርዓተ ቀብር ተጨማሪ ፎቶዎች










