በኮሮና ቫይረስ የተጠረጠሩ 14 ሰዎች ማቆያ እንዲገቡ ተደረገ
በኮሮና ቫይረስ ኢትዮጵያ ውስጥ የተጠረጠሩት ቁጥር 14 ደርሷል
ከቻይና የሚመጡ መንገዶች በቦሌ ለብቻቸው እንዲስተናገዱ ተወሰነ
ኢዛ (ዓርብ ጥር ፳፱ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. February 7, 2020)፦ የኮሮና ቫይረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ሊገባ ይችላል የሚል ሥጋት እየበረከተ ባለበት ወቅት እስካሁን በቫይረሱ የመያዝ ምልክት ያሳዩ 14 ሰዎች በለይቶ ማቆያ ሥፍራ እንዲገቡ ተደርጓል።
በወቅታዊው የኮረና ቫይረስና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ዛሬ ጥር 29 ቀን 2012 ዓ.ም. በተሠጠ ሳምንታዊ መግለጫ ላይ እስካሁን 29 ጥቆማዎች ለኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ደርሷል።
በጥቆማው መሠረት በ29ኙ ላይ በተደረገ ማጣራት 14ቱ በቫይረሱ የመያዝ ምልክት በማሳየታቸው ተለይተው ወደ ማቆያ ስፍራ እንዲገቡ መደረጉን ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል። ከእነዚህ ውስጥ የመጀመሪያዎቹ አራቱ ተጠርጣሪዎች መኖራቸውን ጥር 19 ቀን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በሠጡት መግለጫ ያስታወቋቸው ሲሆኑ፣ ሌሎቹ አራቱ ደግሞ ጥር 25 ቀን መግለጫ የተሠጠባቸው ናቸው። ቀሪዎቹ ስድስቶቹ ደግሞ በዛሬው ዕለት ለሦስተኛ ጊዜ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በሠጠው መግለጫ ለሕዝብ ይፋ ያደረገው አዲስ የተገኙ ተጠርጣሪዎች ሲሆኑ፤ በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ እስከዛሬው ዕለት የተጠርጣሪዎቹን ቁጥር ወደ 14 ከፍ እንዲል ያደረጉት መኾናቸው ታውቋል።
ከ14ቱ ተጠርጣሪዎች ውስጥ የአሥራ አንዱ ተጠርጣሪዎች የደም ናሙናዎች ወደ ደቡብ አፍሪካ ስለመላካቸው የሚያትተው የኢንስቲትዩቱ መረጃ፤ ከእነዚህ ውስጥ ስምንቱ ከቫይረሱ ነፃ መኾናቸው መረጋገጡን ያስረዳል። የቀሪዎቹ የሦስቱ ተጠርጣሪዎች የደም ናሙና ወደ ደቡብ አፍሪካ ተልኮ የምርመራው ውጤት እየተጠበቀ ነው ተብሏል። ሌሎቹ ሦስቱ ናሙናዎች ደግሞ ለምርመራ እንደሚላክ ተገልጿል።
ዛሬ ከተሠጠው መግለጫ መረዳት እንደተቻለው፤ ከቻይና ዉሃን ከተማ የሚመጡ ማናቸውም መንገደኞች ወደ ላፍቶ ማቆያ ማዕከል እንዲገቡ ተወስኗል። ከአሥራ አራቱ ተጠርጣሪዎች ውስጥ አሥራ ሁለቱ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፣ ሁለቱ ቻይናውያን መኾናቸው ታውቋል።
ከዚህ ውሳኔ ሌላ ከየትኛውም የቻይና ግዛት የሚመጡ መንገደኞች አዲስ አበባ ሲደርሱ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከሌሎች መንገደኞች ሳይቀላቀሉ የሙቀት ምርመራ የሚደረግላቸው እንደኾነም ተጠቅሷል።
እንዲህ ያለው አሠራር ከቻይና የሚመጡ መንገደኞች ብቻ የሚስተናገዱበት ልዩ የኢሚግሬሽን መስኮት እንዲሰናዳ በማድረግ ምርመራውን በማጥበቅ እየተሠራ እንደኾነም ተገልጿል።
መንግሥት ካለው ስጋት አንጻር እንዲህ ባለው መልኩ ቫይረሱን ለመቆጣጠር እየተሠራ ቢኾንም፤ በሌላ በኩል በሳምንት 35 በረራዎችን ወደ ቻይና የሚያደረገው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዬን አላቋርጥም ብሏል። እስከትናንት ድረስ ባለ መረጃ ከ31 ሺህ 500 በላይ (31,524) ሰዎች በዓለም ላይ በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን፣ ከአንድ ሳምንት በፊት ከነበረው ጋር ሲወዳደር ከ122 በመቶ በላይ መጨመሩ ታውቋል። ከሳምንት በፊት በቫይረሱ የተያዙት ቁጥር ከ14 ሺህ ሰዎች በላይ እንደነበሩ ይታወቃል።
31,524 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን በሚያሳየውና ትናንት በወጣው መረጃ እንደተጠቆመው፤ ከእነዚህ በቫይረሱ ከተያዙት ውስጥ 15 በመቶ ወይም 4 ሺህ 825 ሰዎች አስጊ ሁኔታ ላይ መኾናቸው ታውቋል። በመረጃው መሠረት እስከ ትናንት ድረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 638 ደርሷል። ያገገሙት ደግሞ 1,652 እንደኾኑ ተገልጿል። የኮሮና ቫይረስ ቫይረስ መነሻ ዉሃን የተባለቸው የቻይና ግዛት መኾኗ ይታወቃል። (ኢዛ)



