Prof. Berhanu Nega

ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ

“ብልጽግና የመንግሥትና የፓርቲውን ገንዘብና ሀብት ማደበላለቅ የለበትም” ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ

ኢዛ (ረቡዕ የካቲት ፲፰ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. February 26, 2020)፦ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) በአገራዊ ለውጡ ሒደትና በቀጣዩ ምርጫ 2012 ዙሪያ ያለውን ሥጋት ያንጸባረቀበት፣ የብልጽግና ፓርቲን አንዳንድ አካሔዶች አደገኛነት ጭምር የጠቀሰበትን አቋም በፓርቲው መሪ በኩል ዛሬ ይፋ አድርጓል።

የኢዜማ መሪ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ዛሬ የካቲት 18 ቀን 2012 ዓ.ም. ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ባስተላለፉት መልእክት (ይህ መልእክት በእስርሳቸው ሲነበብ አንድ ሰዓት የፈጀ ነበር)፤ ተስፋ የተደረገበት ለውጥ እንዳይደናቀፍ፤ እንዲሁም ቀጣዩ ምርጫ ፍትሐዊ ይኾን ዘንድ ሁሉም የሕብረተሰቡ ክፍል ሊኖርበት የሚገባውን ኃላፊነት በዝርዝር የቀረበበት ነው።

“የኢትዮጵያ የለውጥ ሒደት፣ የቀጣሁ ምርጫ አገራዊ ፋይዳና የተደቀኑ አደጋዎች” የሚል ርዕስ ያለውና በኢዜማ መሪ የተላለፈው 19 ገጾች ያሉት መልእክት፤ በተለይ ከዚህ ቀደም ብርቱ ተቃውሞ የነበረበትን የፓርቲውንና የመንግሥትን ሀብት በማደበላለቅ የሕዝብ ሀብትን ለፓርቲ መጠቀሚያ ማድረግ እየታየ መኾኑንም ያመለከተ ጭምር ነው።

ይህንንም፤ “በዚህ ሒደት የመንግሥትና የፓርቲ ኃላፊነቶችን የሚያደበላልቁ እርምጃዎች ማየታችን እጅግ አሳሳቢ ነው” በማለት የኢዜማ መሪ ገልጸዋል። ይህ በተጨባጭ መረጃ የሚቀርብ መኾኑን ጭምር በመግለጽ፤ ቀጣዩን ምርጫ ፍትሐዊ እንዳይኾን ጋሬጣ እንደሚኾን ፓርቲያቸው ያለውን ሥጋት ፕ/ር ብርሃኑ በዚሁ መልእክታቸው ላይ ተናግረዋል።

“እንዲህ ያሉት አካሔዶች እርምት ካልተወሰደባቸው የምርጫውን አካሔድ ክፉኛ ሊያበላሹና ወደምንፈራው ሥርዓት አልበኝነት ወይንም ወደ አዲስ ዐይነት አምባገነናዊ ሥርዓት ሊወስዱን ይችላሉ” በማለት፤ ኢዜማ በዚሁ የዛሬው መልእክቱ አስታውቋል።

ኢዜማ እንዲህ ባለው ሁኔታ ብልጽግናና መንግሥትን በይፋ ጠንከር ያለ ሒስ ሲሠጥ የመጀመሪያው ነው እየተባለ ሲሆን፣ የፓርቲናና የመንግሥትን ኃላፊነት በመደበላለቅ እየተፈጸመ ያለውን ተግባር የማስቆሙ ኃላፊነት የብልጽግና ፓርቲ ብቻ ሳይሆን፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጭምር እንደኾነም ይጠቅሳል የመሪው መልእክት።

ይህንንም፤ “ምርጫውን ነጻና ፍትሐዊ የማድረግ ኃላፊነት ያለበት ምርጫ ቦርድ፤ እንዲህ ያሉ የምርጫን ፍትሐዊነትና ዴሞክራሲያዊ ሒደት የሚያዛቡ ኹነቶችን በጥንቃቄ መመልከትና ማስተካከያ እርምጃዎችን በፍጥነት መውሰድ ካልቻለ/ካልፈለገ፤ እሱም (ምርጫ ቦርድ) ትልቅ አገራዊ ፕሮጀክት እንዳይሳካ ግዴታውን ባለመወጣት፤ በኢትዮጵያ ሕዝብም በታሪክም ትዝብት ውስጥ መወደቁ አይቀርም” በማለት ገልጾታል።

ሰፊ ይዘት ያለው ይህ የኢዜማ መሪ መልእክት፤ በምርጫው ሒደት ላይ ሥጋት እንዳለው ሁሉ ገልጿል። ጽንፈኛ ቡድኖችም “ሃይ!” ሊባሉ ካልቻሉ፤ የአገሪቱን ችግር ያብሳል፤ ምርጫውንም በአግባቡ ለማድረግ ይቸግራል ብሏል።

ፓርቲዎችና መንግሥት በቅድሚያ ሰላምና ብሔራዊ መግባባት እንዲኖር ያሳሰበበትም ነው። አሁን ያለው ሁኔታም፤ ሕዝቡን ሥጋት ላይ ስለመጣሉ የጠቆመው ይህ መልእክት፤ በሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችንም ያካተተ ነበር። ፕ/ር ብርሃኑ ያስተላለፉት ባለ 19 ገጽ መልእክት ለማንበብ እዚህ ይጫኑ! (ኢዛ) 

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ